የሩሲያ የኒዩክሌርና የኬሚካል መከላከያ ሃይል መሪ በሞስኮ ተገደሉ
ሌተናል ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ በኤሌክትሪክ ሞተር ተደብቆ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ነው ህይወታቸው ያለፈው
ኪሪሎቭ በብሪታንያ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሲሆን፥ ዩክሬንም ትናንት በሌሉበት ከሳቸው ነበር
የሩሲያ ጦር ከፍተኛ አዛዥ በሞስኮ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ መገደላቸው ተነገረ።
በሀገሪቱ ጦር ስር ያለው የኒዩክሌር፣ ባዮሎጂካል እና ኬሚካል መከላከያ ሀይል መሪው ሌተናል ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ በኤሌክትሪክ ሞተር ተደብቆ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ነው ህይወታቸው ያለፈው።
ቦምቡ የተጠመደው ከክሬምሊን በ7 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አፓርትመንት ላይ መሆኑንም የሩሲያ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል።
በፍንዳታው ስማቸው ያልተጠቀሰ የኪሪሎቭ አጋዥም መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፥ የሩሲያ የምርመራ ኮሚቴ ግድያውን መመርመር መጀመሩ ተገልጿል።
የፎረንሲክ ባለሙያዎችም በስፍራው ተገኝተው ምርመራው መቀጠሉና ውጤቱ በአጭር ጊዜ ይፋ እንደሚደረግም ነው የተዘገበው።
ኪሪሎቭ የሚመሩት ሃይል የኒዩክሌር፣ ኬሚካል እና ባዮሎጂካል ጥቃቶች ሲደርሱ ፈጥኖ በመድረስ ዜጎችን ለመታደግ የሚሰራ ልዩ ሃይል ነው።
ይሁን እንጂ ከመከላከል ባሻገር በማጥቃቱ ላይም ተሰማርቷል ስትል ዩክሬን ትከሳለች። ሞስኮ ግን ክሱን አትቀበለውም።
የዩክሬን የደህንነት ተቋም (ኤስቢዩ) ዛሬ በቦምብ ህይወታቸውን ያጡትን የሩሲያ ጀነራል የተከለከሉ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች እንዲተኮሱ አዘዋል በማለት ትናንት በሌሉበት ክስ መስርቶባቸዋል።
ብሪታንያም በጥቅምት ወር 2024 "የክሬምሊን የተዛባ መረጃን የሚያሰራጩ አፈቀላጤ" ናቸው ባለቻቸው ኪሪሎቭ ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደችው ባለው ጦርነት የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን ልትጠቅም እንደምትችል እስካሁን ያለችው ነገር የለም።
በአንጻሩ ምዕራባውያኑ ለኬቭ ድጋፋቸውን ማጠናከራቸው ሞስኮ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ዝግጁ አድርጋ እንድትጠባበቅ እንዳደረጋት በተደጋጋሚ ገልጻለች።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በትናንትናው እለትም "ምዕራባውያን የሩሲያን ትዕግስት እየተፈታተኑ ወደ ቀይ መስመሯ እየገፋፏት ነው፤ ሞስኮ ማንንም አትታገስም" ማለታቸው ይታወሳል።