አዲሱ የሩሲያ ውሳኔ በአሜሪካ ተደጋጋሚ ለተጣሉ ማዕቀቦች ምላሽ ነው ተብሏል
ሩሲያ ሞርጋን ፍሪማንን ጨምሮ 963 አሜሪካዊያን ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አገደች፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት ካመራች ሶስት ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎም በአሜሪካ አስተባባሪነት በሩሲያ ላይ ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሲሆን ከ300 በላይ ዲፕሎማቶቿ ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት ተባረዋል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሀገራት ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ሩሲያም የአጻፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ነዳጅ ገዢ ሀገራት በሩብል እንዲገዙም ውሳኔ አሳልፋለች፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም ሩሲያ 963 አሜሪካዊያን ወደ ሞስኮ እንዳይገቡ ውሳኔ ያስተላለፈች ሲሆን ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ሰውች መካከል ታዋቂው የሆሊውድ ፊልም ባለሙያ ሞርጋን ፍሪማን፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የቀድሞዋ የነጩ ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ዋነኞቹ ናው፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲሱን ማዕቀብ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሩሲያ ማዕቀቡን የጣለችው በአሜሪካ እየተደረገ ላለው ተከታታይ ማዕቀብ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡