“የሩሲያ ወታደሮች ዶንባስ ግዛትን ወደ “ገሃነም” ቀይረዋታል”- ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ያለምንም ግነት “ዶንባስ ሙሉ በሙሉ ወድሟል” ብለዋል
የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር "ሉሃንስክን ነጻ የማውጣት ፕሮጀክት" በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለዋል
በምስራቅ ዩክሬን መጠነ ሰፊ የአየር ላይና የምድር ጥቃት በመሰንዘር ላይ የሚገኙት የሩሲያ ወታደሮች፤ የዶንባስ ግዛት ማውደማቸው ተገለጸ።
የዩክሬን ባለስልጣናት፤ የሩሲያ ወታደሮች ባካሄዱት የአየር ላይ ድብደባ በርካታ ቤቶች ማውደማቸው እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጥቃቱ ዶንባስን ወደ “ገሃነም” ቀይሮታል ብለዋል።
ድፍን ሶስት ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ በቀሩት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፤ ከሩሲያ ኃይሎች በተተኮሱ ሮኬቶችና መድፎች የበርካቶች ህይወት መቀጠፉንና መሰረተ ልማቶች መውድማቸውም የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የሩስያ አውሮፕላኖችም በዩክሬን ምድር ቦምቦች አዝነቧልም ብለዋል፡፡
የሉሃንስክ ገዥ ሰርሂ ጋይዳይ “የሩሲያ ጦር በሲየቪዬሮዶኔትስክ ከተማ ላይ ከባድ ጥፋት ጀምሯል፣ የተኩሱ መጠን በእጥፍ ጨምሯል፣ የመኖሪያ ሰፈሮችን እየደበደበ ነው፣ ሁሉም ቤቶች እያወደመ ነው” ሲሉ በቴሌግራም ቻናል ባስተላለፉት መልእክት አስፍረዋል።
ጋይዳይ "ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ አናውቅም፣ ምክንያቱም እያንዳንዱን አፓርታማ ውስጥ ማለፍ እና መመልከት ፈጽሞ የማይቻል ነው" በማለትም ነው የውድመቱ አስከፊነት የተለጹት።
ቀደም ሲል የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት ፤ በዶንባስ የሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር 13 ደርሰዋል። ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ‘ምንም ግነት የለውም’ ባሉት የትናንት ምሽት ንግግራቸው "ዶንባስ ሙሉ በሙሉ ወድሟል" ብለዋል።
ሮይተርስ ሪፖርቶቹን በገለልተኛነት ማረጋገጥ ባይችልም፤ ሩሲያ የማስተባበያ ምልሽ ሰጥታለች። “ሲቪሎች ኢላማ አላደረኩም” ብላለች ሩሲያ።
የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ "የሉሃንስክ ህዝቦች ሪፐብሊክ ነጻ የማውጣት ፕሮጀክት" በቅርቡ ይጠናቀቃል ሲሉ ተደምጠዋል።
ሚኒሰትሩ "የሩሲያ ጦር ኃይሎች ከሉጋንስክ እና የዶኔትስክ ህዝቦች ሪፐብሊካኖች የህዝብ ሚሊሻ ክፍሎች ጋር በመሆን በዶንባስ ግዛቶች ላይ ቁጥጥር ማስፋፋታቸውን ቀጥለዋል" ሲሉም አክሏል።
የኢንደስትሪ ማእክል እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዶኔትስክ እና የሉሃንስክ አካባቢዎችን በሞስኮ በሚደገፉ ተገንጣዮች ቁጥጥር ስር መሆናቸው ይታወቃል።
የሩስያ ጦር የዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭን ለመያዝ አለመቻሉን ተከትሎ፤የዶንባስ ግዛት የሩሲያ ወታደራዊ ኃይሎች ዋና ዒላማ ሆና እንደቀጠለች ነው።