ጦሩ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 771 የዩክሬን ወታደሮች እጅ መስጠታቸውን አስታውቋል
የሩሲያ ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት እጅ የሰጡትን 771 ወታደሮች ጨምሮ እስካሁን 1 ሺ 730 የዩክሬን ወታደሮች እጅ መስጠታቸውን አስታወቀ፡፡
ወታደሮቹ በጦርነቱ በወደመችው ማሪዎፖል ከተማ በሚገኘው በግዙፉ አዞቭስቶፕል ብረት ፋብሪካ መሽገው ሲዋጉ የነበሩ ናቸው፡፡
ጦሩ ከ771ዱ 80ዎቹ የተጎዱ መሆናቸውንና በኖቫዞቭስክና በዶኔስክ ህክምና እያገኙ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ጥቂት የማይባሉና ከአዞቭስታል የለቀቁ የዩክሬን ወታደሮችን በሃገራቱ ጥያቄ መሰረት በመመዝገብ ላይ እንደሚገኝም ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር (ICRC) አስታውቋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በፋብሪካው መሽገው ከሩሲያ ጦር ሲዋጉ የነበሩት ወታደሮቹ ረጅም ቀናትን በከበባ ቀለበት ውስጥ ሆነው አሳልፈዋል፡፡
የሩሲያ ሁኔታ አስግቶናል ያሉ ፊንላንዳውያን በገፍ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየወሰዱ ነው
ሆኖም የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ተወጥተዋል ያለው የሃገራቸው መንግስት ህይወታቸውን ለማትረፍ በሚል እጅ እንዲሰጡ እና ህክምናና ሌሎችንም ድጋፎች እንዲያገኙ ባዘዘው መሰረት እጅ መስጠት ጀምረዋል፡፡
ወታደሮቹን የእስረኞች ልውውጥ ሊኖር እንደሚችል በማሰብ እጅ መስጠታቸውም ነው የተነገረው፡፡
ሆኖም እጅ ሰጡ የተባሉትን የዛሬዎቹን ወታደሮች በተመለከተ የፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ መንግስት ያለው ነገር የለም፡፡
ዜሌንስኪ ወታደሮቹን በተመለከተ ከሩሲያ ጋር የተጀመረው ድርድር መቀጠሉን ትናንት ረቡዕ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡