ደቡብ ኮሪያ ዩክሬንን ከማስታጠቅ ካልታቀበች ሩሲያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለሰሜን ኮሪያ ልትሰጥ እንደምትችል አስጠንቅቃለች
ሩሲያ ሰሜን ኮሪያን ልታስታጥቅ እንደምትችል አስጠነቀቀች።
አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ላይ መሆናቸው ይታወሳል።
አሜሪካ ወዳጅ የምትላቸውን ሀገራት በማግባባት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንዲለግሱ በማድረግ ላይ ናት።
ደቡብ ኮሪያ የአሜሪካ ወዳጅ ሀገር ስትሆን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንድትሰጥ ማግባባቷ ተገልጿል።
ደቡብ ኮሪያም ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለመስጠት ሁኔታዎችን እየገመገመች መሆኑን ከሰሞኑ አስታውቃለች።
ሩሲያ ዛሬ ባወጣችው መግለጫ ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንዳትሰጥ አስጠንቅቃለች።
ደቡብ ኮሪያ የሩሲያን ማስጠንቀቂያ ችላ ብላ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ከሰጠች ሞስኮ ለሰሜን ኮሪያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እንደምታስታጥቅ ገልጻለች።
የሩሲያ ጸጥታ ምክር ቤት ምክትል ሀላፊ እና የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ድሚትሪ ሜድቬዴቭ እንዳሉት ደቡብ ኮሪያ ከድርጊቷ እንድትታቀብ አስጠንቅቀዋል።
እንደ ራሺያ ቱዴይ ዘገባ ከሆነ ሰሜን ኮሪያ የሩሲያን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንድትታጠቅ በማድረግ የደቡብ ኮሪያን ብሄራዊ ደህንነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ልናደርግ እንችላለን ሲሉም ሜድቬዴቭ ተናግረዋል።
እስራኤል ለዩክሬን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እሰጣለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ እስራኤል እንዳለችው ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ከሰጠች በሶሪያ ያለው የሩሲያ ጦር እርምጃ ይወስዳል ማለቷን ተከትሎ እስራኤል የሩሲያን ደህንነት የሚፈታተን የጦር መሳሪያ ለዩክሬን ከመስጠት መታቀቧ ይታወሳል።