የሩሲያና ቻይና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በአላስካ ግዛት ዙሪያ የጋራ ቅኝት አደረጉ
አሜሪካና ካናዳ የሞስኮና ቤጂንግ አውሮፕላኖችን ማባረራቸውን አስታውቀዋል
ሩሲያ የጋራ ቅኝቱ “የሶስተኛ ወገን ላይ ያነጣጠረ አይደለም” ብላለች
የሩሲያና ቻይና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በአሜሪካ አላስካ ግዛት ዙሪያ የጋራ ቅኝት አደረጉ።
በሰሜን ፓሲፊክ እና አርክቲክ አካባቢ የተደረገው የጋራ ቅኝት አሜሪካ እና ካናዳ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡም አስገድዷል ተብሏል።
የሩሲያው “ቲዩ-95ኤምኤስ” እና የቻይና “ሽያን ኤች6” ኒዩክሌር የጦር መሳሪያ መሸከም የሚችሉ አውሮፕላኖች የተሳተፉበት ቅኝት አራት ስአት የወሰደና አብራሪዎች በተለያዩ ዘርፎች የጋራ ልምምድ ያደረጉበት ነበር ብሏል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር።
ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹ በሩሲያ “ሱ35ኤስ” እና “ሱ-30ኤስኤም” ተዋጊ ጄትች ታጅበው እንደነበር ተገልጿል።
ቅኝቱ የሌላ ሀገርን የአየር ክልል ያልጣሰና “ሶስተኛ ወገን”ን ለመጉዳት ያለመ አይደለም ብሏል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር።
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴርም “ልምምዱ አሁን ካለው ወቅታዊ የአለማቀፍ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ አይደለም” የሚል መግለጫን አውጥቷል።
የአሜሪካ የሰሜን አሜሪካ የአየር መከላከያ እዝ በምህጻሩ “ኖራድ” ግን የሩሲያ እና ቻይና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን አቅጣጫቸውን ቀይረው ወደመጡበት እንዲመለሱ ማድረጉን ነው ያስታወቀው።
አውሮፕላኖቹን በመመለሱ ሂደት የካናዳ አውሮፕላኖች መሳተፋቸውንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የሞስኮ እና ቤጂንግ የጋራ ቅኝትና ልምምድ የአሜሪካንም ሆነ የካናዳን የአየር ክልል ያልጣሰ ቢሆንም ጠንካራ ክትትል እንደሚያደርጉ ሀገራቱ ያወጡት መግለጫ አመላክቷል።
ቻይና እና ሩሲያ ከቅርብ አመታት ወዲህ የምዕራባውያን መር የአለም ስርአትን ለመቀየር ትብብራቸውን በማጠናከር ላይ ናቸው።
ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን ጦርነት ከከፈተች በኋላም ከቤጂንግ ጋር ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ግንኙነታቸው ተጠናክሯል።
በግንቦት ወር በቻይና ጉብኝት ያደረጉት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቅርቡም በካዛኪስታን ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር መገናኘታቸው የሚታወስ ነው።