የተወሰኑ ፊኛዎች በጥብቅ በሚጠበቀው የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አካባቢ መውደቃቸው ተገልጿል
ሰሜን ኮሪያ በቆሻሻ የተሞሉ ፊኛዎችን ወደ ጎረቤቷ መላኳን ቀጥላለች።
በ24 ስአት ውስጥ 500 የሚጠጉ ፊኛዎች ወደ ደቡብ ኮሪያ መግባታቸውን የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሲኡል የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ያረፉት በቆሻሻ የተሞሉ ፊኛዎች በረራዎችን ማስተጓጎላቸው ነው የተገለጸው።
ጊምቦ የተሰኘው አውሮፕላን ማረፊያ ትናንት ምሽት ለሁለት ስአታት አውሮፕላኖችን ማሳረፍና ማስነሳት ተቸግሮ እንደነበር የኮሪያ የኤርፖርት ኮርፖሬሽን ገልጿል።
የደቡብ ኮሪያ ዋነኛው አውሮፕላን ማረፊያ ኢንቺዮንም በረራ ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኖበት እንደነበር አስታውቋል።
ከሴኡል በቅርብ ርቀት በምትገኘው ጊዮንጂ በተባለች ግዛትም በቆሻሻ የተሞላ ፊኛ በአንድ የመኖሪያ ህንጻ ላይ የእሳት ቃጠሎ ማስነሳቱን ነው ሬውተርስ የሀገሪቱን መከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ የዘገበው።
“በፊኛዎቹ ውስጥ በተወሰነ ስአት ልዩነት እሳት የሚፈጥሩ ቁሳቁሶች ስለተደረጉ አደጋው ተፈጥሯል” ብለዋል የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ቃል አቀባይ ሊ ሱንግ ጁን።
ሰሜን ኮሪያ ባለፉት 24 ስአታት ወደ ደቡብ ኮሪያ የላከቻቸው ፊኛዎች አብዛኞቹ በወረቀትና ፕላስቲክ ቆሻሻዎች የተሞሉ ናቸው ተብሏል።
የተወሰኑ ፊኛዎች በጥብቅ በሚጠበቀው የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አካባቢ መውደቃቸውም የሴኡልን የደህንነት አቅም አስገምቷል።
ባለፈው አመት በድሮኖች የደቡብ ኮሪያ መዲናን የቃኘችው ፒዮንግያንግ ለፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል የቆሻሻ ስጦታ መላኳ ሴኡልን በድጋሚ ቢያበሳጭም ምን አይነት ግብረመልስ እንደሚሰጥ ግን አልተገለጸም።
ሰሜን ኮሪያ ወደ ጎረቤቷ በቆሻሻ የተሞሉ ፊኛዎችን መላክ የጀመረችው በሴኡል የተከፈተባትን ፕሮፖጋንዳ ለመቀልበስ እንደሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።
ፒዮንግያንግን ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የገቡ የማህበረሰብ አንቂዎች በጸረ ኪም ጆንግ ኡን በራሪ ወረቀቶች፣ መድሃኒቶች፣ ገንዘብ፣ የደቡብ ኮሪያ ሙዚቃና ቪዲዮ የተሞሉ ፊኛዎችን ወደ ሰሜን ኮሪያ መላካቸው ይታወሳል።
ሴኡል ይህን እንቅስቃሴ እንድታስቆም በተደጋጋሚ ማሳሰቧንና ድርጊቱ አለመቆሙን የምትገልጸው ሰሜን ኮሪያ፥ ባለፉት ወራት በሺዎች የሚቆጠሩ ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎችን በመላክ ተቃውሞዋን አሳይታለች።