ኔታንያሁ በአሜሪካ ኮንግረስ ያደረጉት ንግግር በጋዛ የገጠማቸውን ውድቀት ለመሸፋፈን የሞከረ ነው - ሀማስ
ጋዛን የመቆጣጠር ፍላጎት የለንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጦርነቱ በኋላ እስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘር በማያስቡ ፍልስጤማውያን ይተዳደራል ብለዋል
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ተቃውሞ ያላቸው ዴሞክራቶች በኮንግረሱ አልተገኙም
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንሚን ኔታንያሁ በትላንትናው እለት በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርበው ያደረጉት ንግግር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የመድረስ ፍላጎት እንደሌላቸው አመለካች መሆኑን ሀማስ አስታውቋል፡፡
የሃማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ሳሚ አቡ ዙሃሪ ሀማስ ጦርነቱን ለማቆም አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ጥሪ ተቀብሎ ለመተግበር የእስራኤልን ምላሽ እየተጠባበቀ ነው ብለዋል።
ሆኖም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የትላንትናውን የኮንግረሱ ንግግር ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች ላይ በጦርነቱ የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው አመላክተዋል ነው ያሉት።
አሜሪካ እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል የጦርነት ማቆም የስምምነት ሀሳቡን ትቀበል ዘንድ ተጨማሪ ጫናዎች ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያነሱት።
ኔታንያሁ በአጠቃላይ የስልጣን ዘመናቸው ለአራተኛ ጊዜ በኮንግረሱ ባደረጉት ንግግር በመካከለኛው ምስራቅ ቴልአቪል አሁንም የአሜሪካ ጠንካራ አጋር መሆኗን አስምረው ተናግረዋል፡፡
በተያያዘም ኢራን እና የእጅ አዙር ጦርነት ማከናወኛ ወታደሮቿ ሲሉ የጠሯቸው ሂዝቦላህ እና ሀውቲ በቀጠናው የደቀኑት ስጋት አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም አብራርተዋል።
መካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ላይ ሃማስ ፣ ሂዝቦላህ ፣ ሃውቲ እና ኢራን የደቀኑት ስጋት የተዳፈነ ነገር ግን ለረጂም ጊዜ የዘለቀ ነው ያሉት ኔታንያሁ ጦራቸው በጋዛ በሚያካሂደው ውግያ የሀማስን ሁለንተናዊ አቅም በማዳከም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሀማስ ከፍተኛ ሀላፊ ሳሚ አቡ ዙሀሪ በበኩሉ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር በጋዛ የገጠማቸውን ውድቀት ለመሸፋፈን የሞከረ በውሽት የተሞላ ነው” ብሎታል፡፡
“ኔታንያሁ በጋዛ የተሳካላቸው ነገር ቢኖር ንጹሀንን መግደል እና ማሰቃየት ብቻ ነው” ሲል ከጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር በኋላ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ተናግሯል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን እየተብጠለጠሉባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል ከጦርነቱ በኋላ በጋዛ ስለሚኖረው አስተዳደር የሰነዘሩት ሀሳብ ነው፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ግልጽ ያልሆነ እና ለትርጉም የተጋለጠ መሆኑንም መገናኛ ብዙሀኖቹ እየዘገቡ ነው፡፡
ጋዛን የመቆጣጠር እና የማስተደደር ፍላጎት የለንም ያሉት ኔታንያሁ ከጦርነቱ በኋላ ጋዛ አስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘር በማይፈልጉ ፍልስጤማውያን ይመራል ብለዋል፡፡
ይህን ሀሳባቸው እስራኤል የመረጠችው አስተዳደር ብቻ በጋዛ ይኖራል ማለታቸው ነው በሚል እያነጋገረ ይገኛል፡፡
የፍልስጤም ፕሬዝደንት ቃል አቀባይ ናቢል አቡ ሩድኒህ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት “ፍልስጤማውያን ማን እንደሚያስተዳድራቸው የሚመርጡት እራሳቸው ናቸው ፤ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት የሚሰፍነው ፍልስጤማውያን ምስራቅ እየሩሳሌምን በዋና ከተማነት ሰይመው ነጻ ሀገር ሲሆኑ ብቻ ነው” ብለዋል።