ሞሮኮ ከ2 ስአት በኋላ በተሻረ ጎል አርጀንቲናን አሸነፈች
የፓሪስ ኦሎምፒክ የእግርኳስ ውድድር ሲጀመር የደጋፊዎች ብጥብጥ ለረጅም ጊዜ ጨዋታ እንዲቋረጥ አድርጓል
ተመልካቾች ከስታዲየም ወጥተው ጨዋታው ሲቀጥል አርጀንቲናን አቻ ያደረገችው በቪኤአር ተሽራለች
የፓሪሱ ኦሎምፒክ የወንዶች እግርኳስ ውድድር ትናንት ምሽት ሲጀመር ሞሮኮ በአወዛጋቢ ሁኔታም ቢሆን አሸንፋለች።
በሴንት ኢቴን ስታዲየም በተደረገው የሁለት ጊዜ የእዕሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቷን የገጠሙት የአትላስ አናብስቱ 2 ለ በሆነ ውጤን ነው ያሸነፉት።
ለሞሮኮ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ለኤምሬትሱ አል አይን የሚጫወተው ሱፊያን ራሂሚ ነው።
የምሽቱን የአርጀንቲና እና ሞሮኮ ጨዋታ የደጋፊዎች ብጥብጥ ለሁለት ስአት ገደማ እንዲቋረጥ አድርጎታል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ክርስቲያን መዲና ለአርጀንቲና አቻ የሚያደርግ ጎል ማስቆጠሩን ተከትሎ የሞሮኮ ደጋፊዎች ወደሜዳ ሲገቡና የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ሲወረውሩ ታይተዋል።
ከሁለት ስአት ገደማ በኋላ ሁሉም ደጋፊዎች ከሜዳ እንዲወጡ ተደርጎ በባዶ ስታዲየም ጨዋታው ሊቀጥል ሲል የመሃል ዳኛው በቪዲዮ በታገዘ ዳኝነት (ቪኤአር) የመዲናን ጎል ሽረዋታል።
በቀሪ ሶስት ደቂቃዎች ምንም ጎል ሳይቆጠርም ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሶስት ነጥቦችን ማግኘት ችላለች።
ውሃ ሰማያዊ ለባሾቹን ከሽንፈት ያላዳነች ጎል የአትሌቲኮ ማድሪዱ አሰልጣኝ ዲያጎ ሲሞኒ ልጅ ጂዩሊያኖ ሲሞኒ አስቆጥሯል።
አርጀንቲና በ2004 እና 2008 የኦሎምፒክ እግርኳስ ውድድሮችን ማሸነፏ ይታወሳል።
እድሜያቸው ከ23 አመት በታች ያሉ ተጫዋቾች በሚሳተፉበት የኦሎምፒክ እግርኳስ ለሶስተኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳልያ ለመውሰድም በቀድሞው የሊቨርፑል አማካይ ዣቪየር ማሻራኖ አሰልጣኝነት ፓሪስ ትገኛለች።
አርጀንቲና እና ሞሮኮ በሚገኙበት ምድብ የተደለደለችው ኢራቅ በተመሳሳይ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ዩክሬንን አሸንፋለች።