ዜለንስኪ ሩሲያ በገና እለት በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ጥቃት ፍጹም "ኢሰብአዊ" ነው ሲሉ ኮነኑ
የዩክሬን አየር ሃይል ሞስኮ በ184 ሚሳኤሎች እና ድሮኖች በዩክሬን የኢነርጂ መሰረተልማቶች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሞክራለች ብሏል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቱን "አጸያፊ" በማለት ያወገዙት ሲሆን፥ ለኬቭ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል
ሩሲያ በገና እለት በዩክሬን የኢነርጂ መሰረተ ልማቶች ላይ በበርካታ ክሩዝ እና ባለስቲክ ሚሳኤሎችና ድሮኖች የፈጸመችው ጥቃት "ኢሰብአዊ" ነው አሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ።
የዩክሬን አየር ሃይል ሩሲያ ከተኮሰቻቸው 184 ሚሳኤሎች እና ድሮኖች 59 ሚሳኤሎችና 54 ድሮኖችን መትቶ መጣሉን አስታውቋል። 52 ድሮኖች ከኢላማቸው አልደረሱም ብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የኬቭን ወታደራዊ ተቋማት ለማንቀሳቀስ ወሳኝ ድርሻ ባላቸው የኢነርጂ ተቋማት ላይ ያነጣጠረው "ግዙፍ ጥቃት" የተሳካ ነበር ማለቱን ሬውተርስ አስነብቧል።
የዩክሬን የኢነርጂ ኩባንያ "ዲቴክ" እንዳስታወቀው ሩሲያ ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት 2024 በዩክሬን የኢነርጂ ተቋማት ላይ 13 ጊዜ ጥቃት መፈጸሟን ገልጿል።
የትናንቱ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃት በዶኔስክ፣ ኬርሰን፣ ካርኪቭና ዲኒፕሮፖአትሮቭስክ የአራት ሰዎችን ህይወት መቅጠፉና በርካቶችን ማቁሰሉን የዩክሬኑ ሰስፒልን ዘግቧል።
ከግማሽ ሚሊየን በላይ የካርኪቭ ክልል ነዋሪዎችም ከሃይል ተቆራርጠው ከባዱን ቅዝቃዜ ያለማሞቂያ ለመግፋት ተገደዋል፤ በመዲናዋ ኬቭ እና ሌሎች ከተሞችም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ተከስቷል።
"ፑቲን በገና እለት ሆን ብሎ ከ70 በላይ በሚሆኑ ሚሳኤሎችና በመቶዎች በሚቆጠሩ ድሮኖች ጥቃት ፈጽሟል፤ ከዚህ በላይ ምን አይነት ኢሰብአዊነት አለ?" ብለዋል ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ።
በጥር ወር መጨረሻ ከዋይትሃውስ የሚወጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ጥቃቱን "አጸያፊ" ብለውታል።
በስልጣን ዘመናቸው ለዩክሬን 175 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግ ያዘዙት ባይደን ከስልጣን ከመነሳታቸው በፊት ለኬቭ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ለሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረባቸውም ተገልጿል።
ባይደንን የሚተኩት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በፍጥነት እንዲቆም ይፈልጋሉ፤ ሞስኮም የሰላም ድርድር ከመጀመሩ በፊት በእጇ የምታስገባቸውን የዩክሬን ይዞታዎች በመጨመር ላይ ናት።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የሚያስተሳስሯትን ጉዳዮች ለመበጠስ ካሳለፈቻቸው ውሳኔዎች መካከል ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የጁሊያን የዘመን ቀመር ጋር ያላትን ትስስር ማቋረጥ አንዱ ነበር።
ኬቭ በ2023 ሞስኮ ከምትከተለው የጁሊያን የዘመን ቀመር በመውጣት የገና በዓል በፊት ከሚከበርበት ታህሳስ 28/29 ወደ ታህሳስ 16 እንዲዛወር ማድረጓ ይታወሳል።
በዚህም ትናንት የዘመን ቀመር (ጎርጎሮሳውያን) ሁለተኛውን የገና በዓል ስታከብር ነው ከሞስኮ ከባድ የሚሳኤል ጥቃት የደረሰባት።