ዘለንስኪ የዩክሬን የኔቶ አባልነት "የሚሳካ ነው" አሉ
ዩክሬን ሩሲያ በድጋሚ እንዳታጠቃት የኔቶ አባል እንድትሆን ወይም የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣት ትፈልጋለች
ሞስኮ በየካቲት 2022 ልዩ ያለችዉን ወታደራዊ ዘመቻ በዩክሬን ላይ እንድትከፍት ምክንያት የሆናት ዩክሬን ኔቶን ልትቀላቀል ትችላለች የሚለው ስጋት ነው
ዘለንስኪ የዩክሬን የኔቶ አባልነት "የሚሳካ ነው" አሉ።
የዩክሬን የኔቶ አባልነት "የሚሳካ ነው"፤ ነገርግን ኪቭ አጋሮቿን ማሳመን ይኖርባታል ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በዛሬው እለት ለዲፕሎማቶች ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።
ዩክሬን ኔቶ የአባልነት ግብዝ እንዲያቀርብላት በተደጋጋሚ ጠይቃለች።
የምዕራባውያን ወታደራዊ ጥምረት የሆነው ኔቶ ዩክሬን አንድ ቀን ወደ ጥምረቱ እንደምትቀላቀል ቢገልጽም መቼ እና እንዴት የሚለውን ግልጽ አላደረገም።
ሞስኮ በየካቲት 2022 ልዩ ያለችዉን ወታደራዊ ዘመቻ በዩክሬን ላይ እንድትከፍት ምክንያት የሆናት ዩክሬን ኔቶን ልትቀላቀል ትችላለች የሚለው ስጋት ነው።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ስምምነት የምትደርስ ከሆነ ሩሲያ በድጋሚ እንዳታጠቃት የኔቶ አባል እንድትሆን ወይም የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣት ትፈልጋለች።
"ዩክሬን ወደ ጥምረቱ የምትቀላቀለው በፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን እንረዳለን" ሲሉ ዘለንስኪ በኪቭ በነበረው ስብሰባ ለዲፕሎማቶች ተናግረዋል።
"የዩክሬን ወደ ጥምረቱ መቀላቀል የሚሳካ ነው፤ ነገርግን ሊሳካ የሚችለው አስፈላጊ በሆኑ በሁሉም መንገዶች ስንታገል ነው።"
ዘለንስኪ አጋሮቻቸው ዩክሬን ለኔቶ ምን እንደምታበረክት እና በጥምረቱ ውስጥ የዩክሬን አባልነት አለምአቀፍ ግንኙነትን እንደሚያረጋጋ ማወቅ አለባቸው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ፕሬዝደንት ዘለንስኪ የአውሮፓ ሀገራት ከሩሲያ ጋር ያለው ጦርነት ካበቃ በኋላ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጧት ጠይቀዋል። ዘለንስኪ እንዳሉት ኪቭ ወደ ኔቶ መቀላቀል የምትፈልገው ሩሲያ በድጋሚ ጥቃት እንዳትሰነዝርባት ነው።
ሩሲያ ጦርነቱ የሚቆመው ኪቭ ኔቶን የመቀላቀል ሀሳቧን ስትተው እና ሩሲያ በከፊል የያዘቻቸውን የምዕራብ ዩክሬን ግዛቶች አሳልፋ ከሰጠች ነው የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች። ነገርግን ዩክሬን ይህን የሩሲያ ቅድመ ሁኔታ እጅ እንደመስጠት እንደምትቆጥረው እና እንደማትቀበለው በተደጋጋሚ ገልጻለች።