በአልኮል ሱስ የተጠመዱና ከምሽግ ወጥቶ መዋጋት የማይፈልጉ የዩክሬን ወታደሮች ተበራክተዋል ተባለ
የስነ ህዝብ ቀውስ ያጋጠማት ዩክሬን ከ25 አመት በታች ያሉ ወጣቶቿን ወደ ውጊያ ለመላክ እያቅማማች ነው
ዩክሬን የወታደሮች መመልመያ እድሜ መነሻን ከ25 ወደ 18 አመት ዝቅ እንድታደርግ በአሜሪካ ጫና እየተደረገባት ነው
ሶስተኛ አመቱን ሊይዝ የተቃረበው የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት የዩክሬን ጦር አባላትን በየጊዜው ከማመናመኑ ባሻገር ጦሩ የውግያ ሞራል የሌላቸው እና በተሰላቹ ወታደሮች ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡
ስር በሰደደ የወታደሮች እጥረት ውስጥ እንደሚገኝ የሚነገርለት ጦር አሁን ላይ ደግሞ እድሜያቸው የገፉ እና በአልኮል ሱስ የተጠመዱ ወታደሮች መበራከት ራስ ምታት ሆኖበታል፡፡
የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ በውግያ ላይ ከሚገኙ የጦር አመራሮች እና አዋጊዎች ባሰባሰበው መረጃ አሁን ላይ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ወታደር በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚገኝ፣ የቀኑን በርካታ ክፍል መጠጥ በመጠጣት የሚያሳልፍ እና ከምሽግ ወጥቶ ለመዋጋት ፍላጎት የሌለው መሆኑን አስነብቧል፡፡
የስነ ህዝብ ቀውስ ባጋጠማት ሀገር የወታደሮች መመልመያ እድሜ መነሻን ከ25 ወደ 18 አመት ዝቅ እንዲያደርጉ ከአሜሪካ ጫና የበረታባቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በውግያ ውጤቶች እና በወታደራዊ የውግያ ሞራል መቀዛቀዝ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ጦሩ በጦርነት ላይ አስፈላጊውን ውጤት ማስመዝግብ በሚያስችለው የአባላት እጥረት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ስለመሆኑ የጦር አመራሮች ይናገራሉ፡፡
በዩክሬን 114ኛ የድንበር መከላከያ ብርጌድ ውስጥ እያገለገለ የሚገኝ አንድ ወታደራዊ መኮንን ለጋዜጣው ሲናገር፤ "በቅርቡ የእኛ ብርጌድ ተጨማሪ 90 ወታደሮች ተልከውለት ነበር ፤ ነገር ግን ከነዚህ ውስጥ 24ቱ ብቻ ወደ ውግያ ስፍራዎች ለመሄድ ፈቃደኛ ሲሆኑ የተቀሩት በእድሜ የገፉ፣ የታመሙ ወይም የአልኮል ሱሰኞች ናቸው” ብሏል፡፡
እነዚህ ወታደሮች ከአንድ ወር በፊት በኪየቭ ወይም በዲኒፕሮ ዙሪያ ህይወታቸውን ሲመሩ የነበሩ በተገቢው መንገድ መሳሪያ መተኮስ የማይችሉ ፣ በደንብ ያልሰለጠኑ እና ያልታጠቁ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡
በዚህ የተነሳም በአየር መቃወሚያ እና በሚሳኤል ማስወንጨፍ እዞች ላይ የተመደቡ ምድብተኞች በቀጥተኛ ውግያ እንዲሳተፉ እየተደረገ ይገኛል ነው የተባለው፡፡
ዘ ጋርዲያን ያነጋገረው ሌላ ወታደራዊ መኮንን "በአሁኑ ወቅት በአማራጭ ማጣት ለውግያ ወደ ግንባር እየተላኩ የሚገኙ ወታደሮች የአየር መከላከያ እንዴት እንደሚሰራ የሚያውቁ አንዳንዶቹም በምዕራቡ ዓለም የሰለጠኑ እና ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ናቸው፤ ነገር ግን በሁኔታዎች አስገዳጅነት ምክንያት ከትክክለኛ ምድባቸው በማንሳት ወደ ውግያ ሜዳ እያሰማራናቸው ነው” ሲል ተናግሯል ፡፡
ዩክሬን በውግያ አወዶች እያጋጠማት የሚገኘውን ቀውስ ለመቅረፍ በሰፊው የብሔራዊ ውትድርና ምልመላ እያደረገች ብትገኝም በርካታዎቹ በጦርነቱ የመፋለም ፍላጎት የላቸውም፡፡
በቅርቡ ከህዝብ በተሰበሰበሰ አስተያየት ድምጽ ከሰጡ ዩክሬናውያን መካከል 46 በመቶ ያህሉ በወታደራዊ ምልመላው ውስጥ ላለመካከት የተለያዩ ጥረቶችን እንደሚያደርጉ እና በዚህም ጸጸት እንደማይሰማቸው ሲናገሩ 29 በመቶዎቹ ይህን ሀሳብ ተቃውመዋል፡፡