የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 178 ቀናት ተቆጥረዋል
የሩሲያ ጦር ፤ በጥቁር ባሕር ኃይል ማዘዣ ጣቢያ ላይ ጥቃት ሊያደርስ እንደነበር የገለጸውን ድሮን መምታቱን አስታወቀ፡፡
ከዚህ በፊት የዩክሬን ጦር በክሬሚያ የሚገኘውን የሩሲያ ጦር መርከብ በድሮን መምታቱን ገልጾ የነበረ ሲሆን ሞስኮ ደግሞ ዛሬ ድሮን መምታቷን ገልጻለች፡፡ ሩሲያ ድሮኑን መምታቷን የገለጸችው በክሬሚያ ግዛት በምትገኘው ሴቫስቶፖል ከተማ ውስጥ ነው፡፡
የሴባስቶፖል ከተማ አስተዳዳሪ ሚካሄል ራዝቮጃቭ፤ ድሮኑ ሩሲያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተላከ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ድሮኑ ተመቶ በወደቀበት አካባቢ ትልቅ ጉዳት እንዳስከተለም ነው አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡
እንደተመታ እና እንደወደቀ የተገለጸው ድሮን በክሬሚያ ያለውን የሩሲያ ባህር ኃይልን ለማጥቃት የተላከ እንደነበር ሞስኮ ገልጻለች፡፡ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ የተቀመጠው ደግሞ በፈረንጆች ሃምሌ 31 ቀን፤ ዩክሬን የሩሲያን የባህር ሃይል በድሮን ማጥቃቃቷ ነው፡፡
የሩሲያ መከላከያ መስሪያ ቤት፤ ዩክሬን ባለፈው ወር የሩሲያን ባህር ኃይል ማጥቃቱን ቀድሞ በመረዳቱ ጥቃቱን ማክሸፉን ገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ አየር ኃይል ድሮኑ ጥቃት ከማድረሱ አስቀድሞ መቶ መጣሉ ነው የተገለጸው፡፡
የድሮኑን መመታት የገለጸው የሩሲያ ጦር ሲሆን፤ ከዩክሬን በኩል እስካሁን የተሰማ ነገር ስለመኖሩ የዜና ምንጮች የጠቀሱት ነገር የለም፡፡
የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 178 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በእስካሁኑ ሂደት የጥራጥሬ ምርቶች ያለምንም ችግር ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ስምምነት ከመደረጉ ውጭ በሀገራቱ መካከል ውጤት ያመጣ ድርድር አልተደረገም፡