አሜሪካ፤ ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን በጉልበት የመጠቅለል እቅዷን ከቀጠለችበት ፈጣን ምላሽ እንወስዳለን ስትልም ዝታለች
ሩሲያ የዩክሬንን ሉዓላዊነት በቀጥታ በመጣስ ግዛቶችን የምትቆጣጠረው በስሯ ያሉ ግዛቶችን ለመጠቅለል የሚያስችላት መሰረት ለመጣል መሆኑን በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የአሜረካ ተልዕኮ ገለጸ፡፡
ተልዕኮው በትዊተር ገጹ ላይ ባጋራው ጽሁፉ “የሩስያን ቀጣይ እርምጃ እናውቃለን”ም ብሏል ፡፡
ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶች በጉልበት የመጠቅለል እቅዷን ከቀጠለችበት ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን በፍጥነት እና በከፍተኛ ሁኔታ ምላሽ እንሰጣለን ሲል ተልዕኮው ዝቷል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ምድር እየሄደችበት ያለው ግዛቶችን የመጠቅለል ወታደራዊ እርምጃ ያሰጋውና አሜሪካና አጋሮቿን በአባልነት ያቀፈው ኔቶ የጦሩን ቁጥር ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ በድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ አማካኝነት በቅርቡ መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ዋና ጸሃፊው “የኔቶን ኃይል እናጠናክረዋለን እንዲሁም የከፍተኛ ዝግጁነት ሀይላችንን ቁጥር ከ 40 ሺህ ወደ 300 ሺህ እናሳድጋለን" ነበር ያሉት፡፡
ሩሲያ በበኩሏ አሜሪካም ሆነ ኔቶ አጋሮቿ በዚህ ጉዳይ ላይ እጃቸው ካስገቡና ወደ እንደ ክሪሚያ ወደ መሳሰሉ ግዛቶች ከተጠጉ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ይጀመራል ስትል ማስጠንቀቋ የሚታወስ ነው፡፡
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ድሚትሪ ሜድቬዴቭ በቅርቡ እንደተናገሩት ኔቶ ወደ ክሪሚያ የሚያደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ “ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት የሚያስነሳ ነው”ም ብለው ነበር፡፡