ቻይና በዚህ የጦር ልምምድ ስትካፈል የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜዋ እንደሆነ ተገልጿል
ቻይና እና ሩሲያን ጨምሮ ስድስት ሀገራት የጦር ልምምድ ሊያደርጉ መሆኑን አስታወቁ፡፡
በሩሲያ ግዛት ይካሄዳል የተባለው የጦር ልምምድ በፈረንጆቹ የፊታችን ነሃሴ 30 እስከ መስከረም አምስት ባሉት ስድስት ቀናት እንደሚካሄድ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ በዚህ የጦርነት ልምምድ ላይ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ቻይና፣ ቤላሩስ፣ ታጃኪስታን፣ ህንድ፣ ሞንጎሊያ እና ሌሎችን ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
በዚህ የጦር ልምምድ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቻይና የአሁኑ የጦር ልምምድ ከወቅቱ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር እንደማይገናኝ ገልጻለች፡፡እነዚህ የምስራቅ ሀገራት የጋራ የጦር ልምምዳቸውን ከአራት ዓመት በፊት ያካሄዱ ሲሆን ቻይና ለሁለተኛ ጊዜ በልምምዱ እንደምትካፈል አስታውቃለች፡፡
ይህ የጋራ የጦርነት ልምምድ በሩሲያ እና ቻይና ድንበር አቅራቢያ ካቦራቭስክ በሚባል ስፍራ እንደሚካሄድ የሩሲያ መከላከያ መረጃ ያወጣው መረጃ ያስረዳል፡፡
እንደ ቻይና መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ከሆነ የዘንድሮው የጋራ የጦር ልምምድ ዓለም አቀፋዊ ትብብሮችን ለማስፋት ያለመ እና እየተከሰቱ ያሉ የደህንነት ስጋቶችን ለማስቆም ያለመ ነው፡፡
ቻይና እና ሩሲያ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚተባበሩባቸውን አጀንዳዎች በየጊዜው እያሰፉ የመጡ ሲሆን ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ከመጀመሯ በፊት ሁለቱ ሀገራት የማይተባበሩባቸው አጀንዳዎች አለመኖራቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ከሁለት ሳምንት በፊት 11 ሀገራትን ያሳተፈ የጋራ የጦር ልምምድ በኢንዶኔዥያ ያካሄደች ሲሆን ከሚቀጥለው ሳምንት በኋላ ደግሞ በእስያ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና ሌሎች የእስያ ሀገራትን ያሳተፈ ወታደራዊ ልምምድ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡