ዩክሬን በበኩሏ ከሩሲያ ከተተኮሰባት 18 ሚሳኤሎች ውስጥ 15ቱን አክሽፌያለሁ ብላለች
ሩሲያ የዩክሬን የጦር መጋዝንን ማውደሟን ገለጸች።
ሩሲያ ጦሯን ለአንድ ሳምንት ለልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን በመላክ የተጀመረው የዩክሬን ጦርነት 15ኛ ወሩ ላይ ይገኛል።
በቀዝቃዛ ወራት ምክንያት ለጊዜው ተቀዛቅዞ የነበረው የሁለቱ ወገኖች ጦርነት እንደ አዲስ ተጀምሯል።
ዩክሬን በክሪሚያ በሚገኝ የነዳጅ ማጠራቀሚያ መጋዝን ላይ ለሰነዘረችው የድሮን ጥቃት ሩሲያ የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ የዩክሬን የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዝን ላይ ጥቃት ማድረሷን አስታውቋል።
በዶንቴስክ ግዛት ክራማቶርስክ አቅራቢያ አለ በተባለ የዩክሬም መጋዝን ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 200 ቶን የሚሆን የጦር መሳሪያ ወድሟል ተብሏል።
ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥም በ82 የዩክሬን ወታደራዊ እዞች ላይ በ115 አካባቢዎች ላይ ጥቃት መድረሱንም መከላከያ ሚንስቴር አስታውቋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ዩክሬን ከሩሲያ ዛሬ ማለዳ ጀምሮ 18 የሚሳኤል ጥቃት እንደተሰነዘረባት ገልጻለች።
ከተተኮሱ 18 ሚሳኤሎችም 15ቱን እንዳከሸፈች ገልጻ ቀሪዎቹ በነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች እና መገልገያ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውቃለች።
የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ በአብዛኛው የዩክሬን ከተሞች በረራዎች መሰረዛቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።