የሰሜኑ ጦርነት በስምምነት እንዲቋጭ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና እና እውቅና ስነስርአት ተካሂዷል
መንግስት ከኦነግ ሽኔ ጋር በታንዛኒያ ድርድር ሊጀምር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደገለጹት ድርድሩ ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ነው የሚጀመረው።
ይህን ድርድር የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አብዝቶ ይፈልገዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተለይ “የወለጋ ህዝብ እፎይ ማለት እንዲችል” ሁሉም ወገን የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያ በተደረሰ ስምምነት እንዲቆም አስተዋጾጽኦ ላደረጉ አካላት በተካሄደ የምስጋና እና እውቅና ስነስርአት ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።
በታንዛኒያው ድርድር የሚሳተፉ ወገኖች ከግጭትና ጦርነት እንዳማናተርፍ በመረዳት ለሰላማዊ ንግግር ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ የጠመንጃ ንግግር ከዚህ በኋላ ሊያበቃ እንደሚገባው አንስተዋል።
በጦርነት የረጅም ዘመን ታሪክ አላት ያሏት ኢትዮጵያ የጦርነትን አውዳሚነት ሩቅ ሳትሄድ ካለፉት ሁለት አመታት ብዙ ተምራለችም ሲሉ አብራርተዋል።
መንግስት ከህወሃት ጋር የነበረውን ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመ የግጭት ማቆም ስምምነት መቋጫ አበጅቶለት ዛሬ በይፋ ሰላሙን የሚያጸና ነው የተባለ የምስጋና ስነስርአት ተካሂዷል።
ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚደረገው ድርድርም እንዲሁ ተመሳሳይ ውጤት የሚገኝበት እንዲሆን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን ያቀረቡት።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሰተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳም ከወራት በፊት በጨፌ ስብሰባ ላይ ለኦነግ ሸኔ የድርድር ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 ግንቦት ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውን "ኦነግ ሸኔ" ቡድን በሽብርተኝትነት መፈረጁ አይዘነጋም።
በተለምዶ “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራውና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ቡድን በርካቶችን ህይወት እንዲጠፋ፣ እንዲፈናቀሉ እና ንብረት እንዲያወድም ከማደረግ በዘለለ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ማጥቃቱንም መንግስት በወቅቱ ገልጿል።
“ሸኔ” በ2013 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 463 ሰዎች ላይ አደጋ ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ጥቃት እየተባባሰ መምጣቱም ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተከታታይ ባወጣቸው መግለጫዎችም በቡድኑ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል የዜጎች ደህንነት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ማመላከቱ ይታወቃል።
ኦነግ ሸኔ በጥር ወር 2015 በምስራቅ ወለጋ በፈጸመው ጥቃት ከ50 በላይ ንጹሃን ዜጎችን መግደላቸውን ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት ማሳወቁም የሚታወስ ነው።