ሩሲያ በዩክሬን ረጅም የኮንክሪት ምሽግ መገንባቷን የሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎች ተለቀዋል
በደቡባዊ የዩክሬን ከተማ ፓሎይ የተገነባው ምሽግ ብቻ 30 ኪሎሜትር ይረዝማል ተብሏል
ቡልጋሪያን የሚያህል ግዛቷ በሩሲያ የተያዘባት ዩክሬን ከምዕራባውያን ፈጣን ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላት እየጠየቀች ነው
ሩሲያ በዩክሬን የተጠናከረ ዘመቻ ለመክፈት መዘጋጀቷን የሚያመላክቱ የሳተላይት ምስሎች ተለቀዋል።
"ካፔላ ስፔስ" በተሰኘው ተቋም ይፋ የተደረጉት ምስሎች ሞስኮ ወታደሮች እና ታንኮቿን ከጥቃት የሚጠብቁ ረጃጅም ኮንክሪት ምሽጎችን መገንባቷን ያሳያል።
ደቡባዊ ዛፓሮዢያ እና የክሬሚያ መግቢያ በኮንክሪት ምሽጎች ታጥረው ያሳያል ምስሉ።
በደቡባዊ የዩክሬን ከተማ ፓሎይ የተገነባው ምሽግ ብቻ 30 ኪሎሜትር እንደሚረዝም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
ምሾጎቹ ሩሲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ለማስፈርና አዲስ ዘመቻ ለመክፈት እንደተዘጋጀችበት ያሳያሉ ተብሏል።
ዩክሬን "የተተኳሽ እጥረት ገጥሞኛል፤ ምዕራባውያን የገቡልኝን ቃል ይፈፅሙ" ባለች ማግስት የታየው የሩሲያ ዝግጅት ለኬቭ ፈታኝ እንደሚሆን ባለሙያዎቾ ያነሳሉ።
የቡልጋሪያን ሰፋት የሚያህል ግዛቴን ከሩሲያ አስመልሳለው ያለችው ኬቭም ሰፊ ዘመቻ ለመክፈት መሰናዶዋ መቀጠሉን ሬውተርስ ይገልፃል።
ይሁን እንጂ ሩሲያ ድንገተኛና ፈጣን ዘመቻ ብትጀምር ምላሽ ለመስጠት መቸገሯ እንደማይቀር ተንታኞች ያነሳሉ።
ከምዕራባውያን ታንኮችና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ያገኘችው ኬቭ የተገባላት ቃል በፍጥነት አለመፈፀሙን በተደጋጋሚ ታነሳለች።
ሞስኮ ወሳኝ በሆኑት ዛፓሮዥያ እና ክሬሚያ የገነባቻቸው ኮንክሪት ምሽጎች ላይ የምታሰፍራቸው ወታደሮችና ከባድ መሳሪያዎችም ከወዲሁ ስጋት መፍጠራቸው አይቀርም።
ዩክሬን የመልሶ ማጥቃቱን የምትጀምርበትን ወቅትም ሆነ በሳተላይት ታዩ ስለተባሉት ምስሎች ምንም አስተያየት አልሰጠችም።