ሩሲያ የቻይና ምርቶችን ለጦር መሳሪያዎቿ በስፋት እየተጠቀመች ነው - ዩክሬን
በተለይም በድሮን እና ታንኮች ላይ የቻይና ግብአቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ማረጋገጧን ነው ኬቭ ያስታወቀችው
ቻይና የወታደራዊ ቁሳቁሶች የወጪ ንግዷ ሃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የሚካሄድ መሆኑን በመጥቀስ ውንጀላውን አስተባብላለች
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ በምታውላቸው የጦር መሳሪያዎች ውስጥ የቻይና ስሪት ግብአቶችን በስፋት እየተጠቀመች መሆኑን ዩክሬን ገልጻለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከፍተኛ አማካሪው ቭላዲስላቭ ቭላሱይክ ለሬውተርስ እንደተናገሩት፥ ከአውደ ውጊያዎች በኋላ በተገኙ የሩሲያ የጦር መሳሪያዎች ውስጥ የቻይና ስሪት ግብአቶች እየተገኙ ነው።
ሞስኮ ከምዕራባውያን በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት የጦር መሳሪያ ግብአቶችን ከአውሮፓ ሀገራት እያገኘች አይደለም ያሉት ቭላዲስላቭ፥ በድሮኖች እኛ ታንኮች ላይ የቤጂንግ ስሪት ተገጣጣሚ ግብአቶችን እየተጠቀመች ነው ብለዋል።
የቻይና ግብአቶች በሩሲያ ታንኮች የእሳት መከላከያ ስርአት ውስጥ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ መቻሉንም አብራርተዋል።
ሬውተርስ ግን መሳሪያዎቹ ከቻይና በቀጥታ ለሩሲያ መሸጣቸውን ማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፥ “ቻይና ሩሲያን ጨምሮ ከየትኛውም የአለም ሀገር ጋር በእኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የንግድ ትብብር አላት፤ የወታደራዊ ቁሳቁሶችን ሽያጭ በተመለከተ ግን ሃላፊነት የተሞላበት አሰራርን ትከተላለች” ብሏል።
ቤጂንግ ለሞስኮ የጦር መሳሪያ ግብአቶችን አቅርባለች መባሉንም አስተባብሏል።
የቮልድሚር ዜለንስኪ አማካሪው ቭላዲስላቭ ቭላሱይክ ግን ለሩሲያ የትኞቹ የቻይና ኩባንያዎች የጦር መሳሪያ ግብአቶቹን እንደሸጡ ለምዕራባውያን አጋሮቻችን አሳውቀናል ነው ያሉት።
የቻይናው የጦር መሳሪያ አምራች “ኖሪንኮ” እና “ጉዋንዡ ኢምፖርት ኤክስፖርት” በዩክሬን ጦርነት የሚውሉ የጦር መሳሪያ ግብአቶችን ለሞስኮ ሽጠዋል ከተባሉት ኩባንያዎች መካከል እንደሚገኙበት በመጥቀስ።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ለሞስኮ ያደላ አቋም ይዛለች በሚል በምዕራባውያኑ የምትወቀሰው ቻይና እስካሁን ለሩሲያ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዳላከናወነች ትገልጻለች።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከንም ባለፈው ወር ቤጂንግ እስካሁን “ቀይ መስመሩን” አላለፈችም ማለታቸው የሚታወስ ነው።