በርሊን ለኬቭ በሰጠቻቸው ሊዮፓርድ 2 ታንኮች ጉዳይ ከሞስኮ ጋር መፋጠጧ ይታወሳል
ሩሲያ ከ20 በላይ የጀርመን ዲፕሎማቶችን ከሀገሯ ማስወጣቷ ተነገረ።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ የጀርመን ዲፕሎማቶች ከሩሲያ እንዲወጡ ስለመደረጉ ቢገልጹም፥ በርሊን ስለጉዳዩ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠችም።
የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ ግን በሞስኮ ከሚገኙ 90 የጀርመን ኤምባሲ ሰራተኞች 34ቱ ከሩሲያ እንዲወጡ ታዘዋል ብሏል።
ጀርመን አስቀድማ ከ20 በላይ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ማባረሯ ይታወሳል።
ለዚህም በምክንያትነት ያነሳችው በኤምባሲው የስለላ ስራ የሚሰሩ ዲፕሎማቶች መበራከት ያሰጋኛል የሚል ነበር ብሏል ሬውተርስ።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበርሊን የተወሰደው እርምጃ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ክፉኛ ይጎዳዋል በሚል በመቃወም አጻፋዊ ውሳኔ መተላለፉን ገልጿል።
የሩሲያ ቀዳሚዋ የነዳጅ ገዥ ሀገር ጀርመን ከዩክሬን ጦርነት መጀመር ወዲህ ከሞስኮ ጋር ግንኙነቷ ሻክሯል።
በርሊን ለኬቭ ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ለመስጠት መስማማቷ የቭላድሚር ፑቲንን ሀገር እጅግ ማስቆጣቱም የሚታወስ ነው።
ታንኮቹን ለዩክሬን መስጠት ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያስገባኛል በሚል ሲያቅማሙ የቆዩት መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ በምዕራባውያኑ ጫና ዘመናዊነታቸው የሚነገርላቸውን ታንኮች ወደ ኬቭ መላካቸው አይዘነጋም።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ሀገራት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከሀገራቸው ማስወጣታቸው ይታወሳል።