ጎግል የመረጃ ፍለጋ ገበያውን በብቸኝነት በመቆጣጠር በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ተባለ
የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ኩባንያው 90 በመቶ የሚሆነውን የበይነ መረብ ፍለጋ ተቆጣጥሯል የሚል ክስ አቅርቦበት ነበር
ጎግል ለአፕል፣ ሳምሰንግ፣ ሞዚላ እና ሌሎች ኩባንያዎች ቢሊዮን ዶላሮች ከፍሎ ብቸኛው የመረጃ ፍለጋ ድር ለመሆን ሞክሯል ተብሏል
የአልፋቤት ንብረት የሆነው ጎግል የበይነ መረብ ፍለጋ ገበያውን በብቸኝነት የተቆጣጠረበት መንገድ ከህግ አግባብ ውጭ መሆኑ ተገለፀ።
በአለማችን ቀዳሚው የመረጃ መፈለጊያ ድር የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ከአራት አመት በፊት ባቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ሚኒስቴሩ ጎግል ተፎካካሪዎቹን ከገበያ አስወጥቶ 90 በመቶ የሚሆነውን የበይነ መረብ ፍለጋ ተቆጣጥሯል የሚል ክስ አቅርቦ ሲታይ ቆይቷል።
በትናንትናው እለትም አሚት ሜህታ የተባሉት አሜሪካዊ ዳኛ ጎግል በተንቀሳቃሽ ስልኮችም ሆነ በሌሎች በይነ መረብ መጎብኛዎች ትልቁ የመረጃ ፍለጋ መሳሪያ ለመሆን በሚል በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ከፍሏል ብለዋል።
ኩባንያው ለአፕል፣ ሳምሰንግ፣ ሞዚላ እና ሌሎች ኩባንያዎች ቢሊዮን ዶላሮች ከፍሎ ብቸኛው የመረጃ ፍለጋ ድር ለመሆን መሞከሩንም በመጥቀስ።
ከመረጃ ፍለጋ ገበያው ባሻገር ከማስታወቂያ ሽያጭ ጋር በተያያዘም ጎግል ተቀናቃኞቹን ያስወጣበት መንገድ ህጋዊ አለመሆኑን ዳኛ አሚት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ጎግል በዓመት ቢያንስ 10 ቢሊዮን ዶላር እየከፈለ የመረጃ ፍለጋ ገበያውን በብቸኝነት ለመቆጣጠር እንደሚሰራ ይናገራሉ።
ይህም ከማስታወቂያዎች በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላሮችን ያለተቀናቃኝ እንዲያገኝ እድል ፈጥሮለታልም ነው የሚሉት።
የተላለፈው ውሳኔ ጎግልንም ሆነ እናት ኩባንያውን አልፋቤት ለከባድ ኪሳራ ሊዳርግ እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል።
ኩባንያው ሊተላለፍበት የሚችለው ቅጣት በቀጣይ በሚደረጉ ችሎቶች ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል።
አልፋቤት በአሜሪካው የዲስትሪክት ዳኛ አሚት ሜህታ የተላለፈውን ውሳኔ ይግባኝ ጠይቆ እንደሚያሽረው አስታውቋል።
ኩባንያው ባወጣው መግለጫ "ውሳኔው ጎግል ምርጥ የፍለጋ ድር መሆኑን እውቅና ይሰጥና ማጠቃለያው ላይ ግን ይህን ምርጥ አገልግሎት በቀላሉ ማድረስ አትችሉም ይላል" ሲል ውሳኔውን ተቃውሟል።
የጎግል ጠበቃ ጆን ሽሚትድላይን ቢሊየኖች የመረጃ መፈለጊያውን የሚመሮጡት ለአጠቃቀም ምቹ በመሆኑና ኩባንያውም ለደንበኞቹ የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ሰለሚያፈስ ነው በሚል ተከራክረዋል።
የአሜሪካው አቃቤ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ ግን ውሳኔው "የትኛውም ግዙፍም ሆነ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኩባንያ ከህግ በታች መሆኑን ያሳየ ነው" በሚል አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
ጎግል በቀጣዩ መስከረም ወር የማስታወቂያ ቴክኖሎጂን በተመለከተ ሌላ ክስ ይጠብቀዋል።
ኩባንያው ከሁለት አመት በፊት የመረጃ ፍለጋ ገበያውን በብቸኝነት ተቆጣጥሮታል በሚል በአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት ተከሶ የ4.2 ቢሊየን ዩሮ ቅጣት እንደተላለፈበት የሚታወስ ነው።
ሜታ፣ አማዞን እና አፕልም እንደ ጎግል ሁሉ ገበያውን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ሞክረዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።