ጎግል ፊቱን ወደ ኒዩክሌር ሃይል አዞረ
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ከአነስተኛ የኒዩክሌር ማብለያዎች ሃይል ለማግኘት “ካይሮስ ፖወር” ከተሰኘ ተቋም ጋር ስምምነት ተፈራርሟል
ጎግል ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመረጃ ማዕከላቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ሃይል እንደሚያስፈልገው ገልጿል
የአልፍቤት ንብረት የሆነው ጎግል ፊቱን ወደ ኒዩክሌር ሃይል ማዙሩ ተነገረ።
ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) የመረጃ ማዕከላቱ ከፍተኛ ሃይል ያስፈልገኛል ያለው ኩባንያው፥ ከአነስተኛ የኒዩክሌር ማብለያዎች የሚገኝ ሃይልን ለመጠቀም ስምምነት ተፈራርሟል።
የአለማችን ቀዳሚው የመረጃ መፈለጊያ ድር ስምምነት የተፈራረመው “ካይሮስ ፓወር” ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ነው።
በስምምነቱ መሰረት ጎግል እስከ 2030 ድረስ ከመጀመሪያው ማብለያ የኒዩክሌር ሃይል ማግኘት የሚጀምር ሲሆን፥ በ2035 በስፋት መጠቀም ይጀምራል ተብሏል።
የጎግል የኒዩክሌር ማብለያ ጣቢያ የት እንደሚገነባና ምን ያህል ወጪ እንደሚደረግበት ግን ኩባንያዎቹ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
የጎግል የኢነርጂ እና የአየርንብረት ጉዳዮች ዳይሬክተር ሚቼል ቴሬል “ስምምነቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚፈልጉትን ከፍተኛ ሃይል በንጹህ እና አስተማማኝ አማራጭ ለመተካት ያስችላል” ብለዋል።
የካይሮስ ፓወር ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ኦልሰን በበኩላቸው ከጉግል ጋር የተደረሰው ስምምነት የኒዩክሌር ሃይልን ለንግድ ስራዎች ለማዋል እና የሃይል አማራጮችን ከካርበን ልቀት የተላቀቁ ለማድረግ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የጎግል እና ካይሮስ ፓወር የኒዩክሌር ስምምነት በአሜሪካ የኒዩክሌር ቁጥጥር ኮሚሽን እና በተለያዩ ተቋማት መጽደቅ ይኖርበታል።
የአሜሪካ የኒዩክሌር ቁጥጥር ባለስልጣናት ባለፈው አመት ተቀማጭነቱን ካሊፎርኒያ ላደረገው ካይሮስ ፓወር ከዚህ ቀደሞቹ የተለየ የኒዩክሌር ማብለያ እንዲገነባ ፈቃድ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይህ ፈቃድ በ50 አመት ውስጥ የመጀመሪያው ነው የተባለ ሲሆን፥ ኩባንያው በሀምሌ ወር 2024 በቴኔስ የኒዩክሌር ማብለያ ማሳያ የሚሆን ግንባታውን መጀመሩን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
የጎልደን ሳችስ መረጃ እንደሚያሳየው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የመረጃ ማዕከላት የሃይል ፍጆታ እስከ 2030 ድረስ በእጥፍ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም ምክንያት ማይክሮሶፍት እና አማዞንን ጨምሮ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በዘላቂነት የሃይል ፍጆታቸውን ሊያገኙበት ወደሚችሉት የኒዩክሌር የሃይል አማራጭ ፊታቸውን እያዞሩ ይገኛሉ።
የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ ባለፈው አመት በአረብ ኤምሬትስ ሲካሄድ አሜሪካ ከኒዩክሌር የሚያገኙትን ሃይል በ2050 በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ቃል የገቡ ሀገራትን ጎራ መቀላቀሏ ይታወሳል።
ተቺዎች ግን የኒዩክሌር ሃይል ከብክለት ሙሉ በሙሉ የጸዳ አይደለም፤ ከረጅም ጊዜ በኋላ አደጋ የሚያደርሱ ቆሻሻዎችን ይፈጥራል በሚል ይከራከራሉ።