ሩሲያ፤ ፈረንሳይና ጀርመን በዩክሬን ግጭት ላይ በሽምግልና ለመሳተፍ ፍላጎት አላሳዩም ስትል ወቀሰች
ፕሬዝዳንት ማክሮን በዩክሬን ጉዳይ ሀገራቸው የአስታራቂ ሚና እንደሚኖራት እርግጠኛ ነኝ ሲሉ እንደነበር ይታወቃል
ሞስኮ፤ ከማክሮን እና ሾልዝ ይልቅ የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ለማሸማገል ያደረጉት ጥረት አደንቃለሁ ብላለች
ሩሲያ፤ ፈረንሳይ እና ጀርመን በዩክሬን ግጭት ላይ በሽምግልና ለመሳተፍ “ፍላጎት አላሳዩም” ስትል ወቀሰች።
በተቃራኒው የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ለማሸማገል ያደረጉት ጥረት እንደምታደንቅ ሞስኮ አስታውቃለች።
ክሬምሊን ሰኞ እንዳስታወቀው ፈረንሳይ እና ጀርመን በዩክሬን ግጭት ላይ በሽምግልና ለመሳተፍ "ፍላጎት የላቸውም" ያለ ሲሆን የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ንግግሮችን ለማደራጀት ያቀረቡትን ሀሳብ አወድሰዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "አንካራ ከፓሪስ እና ከበርሊን የተለየ አቋም ይዛለች፣ እናም የሽምግልና ጥረቱን ለመቀጠል ዝግጁ ናት” ብለዋል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ነገር ግን "የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል እና የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ የሩሲያን አቋም ለማዳመጥ ወይም በሽምግልና ጥረቶች ላይ ለመሳተፍ ምንም ፍላጎት አላሳዩም" ሲሉ ተናግረዋል ቃል አቀባዩ።
ሩሲያ ይህን ብትልም በተለይም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዩክሬን ጉዳይ ፈረንሳይ የአስታራቂ ሚና እንደሚኖራት እርግጠኛ ነኝ ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።
በዚህም ማክሮን ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መወያየታቸው የሚታወቅ ነው።
ይሁን እንጅ ማክሮን የተጓዙበት መንገድ ውጥረቱን ከማርገብ ይልቅ ጥረቶችን የሚጎዳ ነው የሚል ትችት ሲቀርብባቸው እንደነበርም ይታወሳል።
በሳምንቱ መጨረሻ የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ፣ የቱርክ እና የእንግሊዝ አቻዎቻቸውን በስልክ ማናገራቸው ይታወቃል።
ሾይጉ ከሶስቱም ሀገራት ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ "ዩክሬን 'ቆሻሻ ቦምብ (ኒውክሌር)' ከተጠቀመች ሊቀሰቀሱ ስለሚችሉ መዘዞች ያላቸውን ስጋት አስረድተዋል።
ይሁን እንጅ ዩክሬን ቆሻሻ ቦምብ -‘dirty bomb' ልትጠቀም ትችላለች የሚለው ነገር በዩክሬን ላይ የተሰነዘረ የሐሰት ውንጀላ ነው በማለት ዋሽንግተን የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡