ሩሲያ ባደረሰችው ጥቃት ከአንድ ሚሊዮን በላይ አባወራዎች ኤሌክትሪክ አልባ መሆናቸውን ዩክሬን አስታወቀች
የዩክሬን ባለስልጣናት የሩሲያ ጥቃት በአውሮፓ አዲስ የስደተኞች ማዕበል ለመፍጠር ያለመ ነው ብለውታል
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ ሩሲያ 30 በመቶ የዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እንዳወደመች መግለጻቸው ይታወሳል
ሩሲያ በዩክሬን የኢነርጂ መስረተ ልማቶች ላይ "መጠነ ሰፊ ጥቃት" መሰንዘሯን ተከትሎ በአብዛኛውየ ሀገሪቱ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ዩክሬን አስታወቀች፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ኪሪሎ ቲሞሼንኮ በመላ ሀገሪቱ በኢነርጂ ተቋማት ላይ የተፈጸመው የሩስያ የአየር ድብደባ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አባወራዎችን ኤሌክትሪክ አልባ አድርጓቸዋል ብለዋል ።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በሩሲያ በኩል እየተሰነዘረ ያለው ጥቃት እጅግ ከባድ በመሆኑ ለመቋቋም መቸገራቸው ገልጸዋል፡፡
"በእርግጥ እኛ 100 በመቶ የሩስያ ሚሳኤሎችን ለመምታት እና ድሮኖችን ለመምታት ቴክኒካል ችሎታ የለንም፤ እርግጠኛ ነኝ፣ ቀስ በቀስ፣ ያንን እንደምናሳካ፣ በአጋሮቻችን እርዳታ። አሁን፣ አብዛኞቹን የክሩዝ ሚሳኤሎችን፣ አብዛኞቹን ሰው አልባ አውሮፕላኖች እያወረድን ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የዩክሬን ፕሬዝዳንት ረዳት ሚካሂሎ ፖዶሊያክ ጥቃቱ ሞስኮ በአውሮፓ አዲስ የስደተኞች ማዕበል ለመፍጠር እንደምትፈልግ የሚያመላክት ድርጊት ነው ማለታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ሩሲያ በሰነዘረችው ጥቃት በሳምንት ውስጥ 30 በመቶ የዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን መውደማቸው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከቀናት በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ፤ የኢነርጂ መሰረተ ልማትን ተደጋጋሚ ኢላማ ያደረገውን የሩሲያ እርምጃ “የሽብር ጥቃት” ሲሉም ገልጸውታል።
"ከጥቅምት 10 ጀምሮ 30 በመቶው የዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ወድመዋል፤ ይህም በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የኃል መቆራረጥ እንዲፈጠር አድርጓል" ሲሉም ተናግረዋል ዘለንስኪ በትዊትር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት።
ጥቃቱ “ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገዛዝ ጋር ለመደራደር የሚስችል ምንም እድል የለም” እንደማለት ነውም ብለዋል።
ወታደራዊ ተንታኞች በበኩላቸው የወቅቱ የክሬምሊን ባለስልጣናት እርምጃ ሞስኮ በጦር ሜዳ ላይ ለደረሰው ኪሳራ የሰጠችውን ምላሽ ይመስላል ሲሉ ገልጸውታል።
ሩሲያ የኢራን እንደሆኑ በሚነገርላቸው ድሮኖች በመታገዝ በተለያዩ የዩክሬን ከተሞች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመሰንዘር ላይ መሆኗ ይታወቃል።
የአሁን ተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን ሚሳዔሎች ድብደባ የጦርነቱ መጀመሪያ አከባቢ ሞስኮ ኪቭን ለመቆጣጠር ታደርገው የነበረ መጠነ ሰፊ ጥቃት አይነት ነው ተብሏል።