ሩሲያ ውሃን ለመፈለግ ወደ ጨረቃ መንኮራኩር አመጠቀች
የሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ "ሉና-25" የተባለችው መንኮራኩር ከ10 ቀናት ጉዞ በኋላ ጨረቃ ላይ እንደምታርፍ አስታውቋል
የሩሲያ የጨረታ ተልዕኮ ከህንድ ብርቱ ፉክክር ገጥሞታል
ሩሲያ ከ47 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጨረቃ መንኮራኩሯን ልካለች።
የሞስኮ የጨረቃ ጉዞ በደቡባዊ ጫፍ አለ ተብሎ የሚታመነውን የውሃ ክምችት ለማግኘት ሀገራት እያደረጉት ያለው እሽቅድድም አካል መሆኑ ተነግሯል።
የሩሲያ የጨረታ ተልዕኮ ከግማሽ ክፍለ ዘመን ገደማ በኋላ ከህንድ ብርቱ ፉክክር ገጥሞታል።
ህንድ ባለፈው ወር "ቻንደርያን-3" የተባለ መንኮራኩር አምጥቃለች።
የረጅም ዓመት ተፎካካሪዎቿ አሜሪካና ቻይና በጨረቃ ላይ ውሃን የሚፈልጉ ጠንካራ መርሀ-ግብሮች አሏቸው።
"ሉና-25" የተባለችው የሞስኮ መንኮራኩር አርብ ከሞስኮ አምስት ሽህ ኪ.ሜ ከሚርቀው ጣቢያ መነሳቷ ታውቋል።
መንኮራኩሯ በተነሳች በአንድ ሰዓት ውስጥ መሬትን ለቃ ወደ ጨረቃ መምዘግዘጓ ተነግሯል።
የሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ "ሉና-25" ከ10 ቀናት ጉዞ በኋላ ጨረቃ ላይ ታርፋለች። ይሁን እንጂ ኤጀንሲው ቀደም ብሎ የጉዞውን እርዝማኔ 12 ቀን ነው ብሎ ነበር።
የአነስተኛ መኪና ያህል ቁመት ያላት "ሉና-25" ተልዕኮዋን ለማሳካት በደቡባዊው የጨረቃ ክፍል ለአንድ ዓመት እንደምትቆይ ተነግሯል።
ተመራማሪዎች ለክፍለ ዘመናት ከሰሀራ በረሃ በመቶ እጥፍ ደረቃማ በሆነችው ጨረታ ውሃ ለማግኘት ፍለጋ አድርገዋል።
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) በ2018 በጨረቃ ጥቁር ደቡባዊ ክፍል የበረረዶ ክምር ያገኘ ሲሆን፤ በ2020 ደግሞ ብርሃን ባለበት ክፍል ውሃ እንደሚገኝ አረጋግጧል።