ሚስጢራዊው የቻይና መንኮራኩር ከ276 ቀናት በኋላ ወደ መሬት ተመለሰ
ቤጂንግ ዳግም ጥቅም ላይ በሚውሉ መሳሪያዎች የሰራችው ነው የተባለው መንኮራኩር ዝርዝር መገለጫዎቹ ግን አልተጠቀሱም
ቻይና በ2021ም ሚስጢራዊ ሆኖ የቀረ መንኮራኩር ወደ ህዋ ማምጠቋ የሚታወስ ነው
ቻይና ወደ ህዋ ያመጠቀችው መንኮራኩር የሙከራ ጊዜውን አጠናቆ ዛሬ ወደ ምድር ተመልሷል።
ያለሰው የመጠቀው መንኮራኩር ከ276 ቀናት በኋላ ነው በሰሜን ምዕራብ ቻይና ጂኩዋን የህዋ ሳይንስ ማዕከል ያረፈው።
ቤጂንግ ስለመንኮራኩሩ የህዋ ጉዞ አላማ፣ በቆይታው ያሳካቸው ተግባራትና የስራው አይነትን ከመጥቀስ ተቆጥባለች።
በነሃሴ ወር 2022 የመጠቀው መንኮራኩር ከህዋ ላይ ያነሳቸው ምስሎች በቅርቡ ይለቀቃሉ ተብሏል።
ቻይና ስያሜውንም ሆነ ተግባሩን በዝርዝር ያልጠቀሰችው መንኮራኩር ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ የህዋ ቴክኖሎጂዎችን የሞከርኩበት ነው ማለቷን ሲጂቲኤን አስነብቧል።
ቤጂንግ በ2021ም ወደ ህዋ የላከችው መንኮራኩር ጉዳይ መነጋገሪያ መሆኑ አይዘነጋም።
የህዋ ቆይታውን አጠናቆ ወደ ምድር የተመለሰው መንኮራኩር የነበረው ተልዕኮ በግልፅ አለመታወቁ በተለይ ከአሜሪካ በኩል ጥያቄ ማስነሳቱን ሬውተርስ አስታውሷል።
ቻይና እንደ አሜሪካው "X-37B" አይነት ግዙፍ መንኮራኩር መስራቷን ተንታኞች ይናገራሉ።
"X-37B" በህዋ ላይ ለአመታት መቆየት የሚችል መንኮራኩር መሆኑን ባለሙያዎች ያነሳሉ።
ይሄው የአሜሪካ መንኮራኩር ከ900 ቀናት ቆይታ በኋላ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ህዳር ወር መመለሱ ተነግሯል።
ሀያላኑ ሀገራት በህዋ ላይ መሬትን የሚቃኙ፣ የመገናኛና የአየር ትንበያ የሚውሉ ማሽኖችን የያዙ መንኮራኩሮችን በሚስጢራዊ መንገድ ማምጠቃቸውን ቀጥለዋል።