የአሜሪካ አየር ሀይል አዛዥ ሩሲያ የረጅም ጊዜ የዋሸንግተን ተገዳዳሪ ሀገር ትሆናለች ብለዋል
የሩሲያ ጦር ከዩክሬን ጦርነት በፊት ከነበረው የበለጠ ጠንካራ መሆኑን አሜሪካ ገለጸች፡፡
የዓለማችን ቁጥር አንድ ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ የሩሲያ ጦር አሁንም ጠንካራ መሆኑን ተናግራለች፡፡
በአሜሪካ አየር ሀይል የአውሮፓ እና አፍሪካ ዋና አዛዥ ጀነራል ጀምስ ሄከር እንዳሉት የሩሲያ ጦር ከዩክሬን ጦርነት በፊት ከነበረው የበለጠ ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጀነራል ጀምስ በዓመታዊ የአየር ሀይል እና ጠፈር ሳይነስ ገባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የሩሲያ ጦር አሁንም ከነ ጥንካሬው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከ100 በላይ የሩሲያ አውሮፕላኖች በዩክሬን ተመተዋል ቢባልም አሁንም የሩሲያ ጦር ጠንካራ ነው ያሉት አዛዡ ሩሲያ የአሜሪካ የረጅም ጊዜ ተገዳዳሪ ሀይል ትሆናለች ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ እንደዘገበው ከሆነ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ሩሲያ 350 ሺህ ያህል ወታደሮቿን በሞት እና በአካል መጉደል አጥታለች፡፡
አሜሪካን 50 ቢሊየን ዶላር ያሳጡት አፍሪካውያን ዲጂታል አጭበርባሪዎች
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን 180 ሺህ አዲስ ወታደሮች ጦሩን እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ ህግ መፈረማቸውን ተከትሎ ሞስኮ በአጠቃላይ ያላት ጦር ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን አድጓል፡፡
ሩሲያ ከቻይና በመቀጠል ግዙፍ ጦር ያላት ሁለተኛዋ የዓለማችን ሀገር መሆን ችላለችም ተብሏል፡፡
ጀነራል ጀምስ አክለውም አሜሪካ እጅግ ውድ የሆኑ የስለላ እና የደህንነት አውሮፕላኖች መጠቀም ልታቆም እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ ዶላር የሚወጡ ሰው አልባ ድሮኖችን ከመጠቀም ርካሽ እና የተሸለ መረጃ ሊሰጡ በሚችሉ ድሮኖች መቀየር ይገባልም ብለዋል፡፡
አፍሪኮም የተሰኘው የአሜሪካ አየር ሀይል ዋና አፍሪካ ማዘዣ ለስለላ እና ደህንነት ስራዎች 40 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሰው አልባ አውሮፕላን ስትጠቀም እንደነበር ነገር ግን ይህ አዋጭ እንዳልሆነ ጀነራሉ ጠቁመዋል፡፡
ጀነራል ጀምስ አክለውም በዩክሬን ጦርነት ወቅት ውድ ያልሆኑ የስለላ እና ወታደራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተሞክረው ውጤታማ እየሆኑ በመሆኑ አሜሪካም ይሄንን ልትጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡