አሜሪካን 50 ቢሊየን ዶላር ያሳጡት አፍሪካውያን ዲጂታል አጭበርባሪዎች
መቀመጫቸውን ናይጄርያና ጋናን በመሳሳሉ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ያደረጉት አጭበርባሪዎች ተደራሽነታቸው እየሰፋ ይገኛል
አጭበርባሪዎቹ “እየሰራን ያለነው አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት ዘመን የዘረፉትን ንብረት ማስመለስ ነው” ይላሉ
አለም በቴክኖሎጂ እና በኢንተርኔት አማካኝነት እጅጉን እየተቀራረበች በምትገኝበት ጊዜ በበይነ መረብ አማካኝነት የሚደረጉ የዲጂታል ማጭበርበሮች እየጨመሩ ይገኛሉ።
በተለይ ከምዕራብ አፍሪካ መነሻቸውን ያደረጉ የዲጂታል ማጭበርበሮች ከአፍሪካ ተሸግረው በአውሮፓ እና አሜሪካ እንዲሁም በሌሎች የአለም ክፍሎች ያላቸው ተጽዕኖ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝ ይነገራል።
እነዚህ አጭበርባሪዎች ከራሳቸው አልፎ ሌሎች ወጣቶችን በማሰልጠን በዲጂታል ማጭበርበር ላይ በሰፊው እያሰማሩ ነው።
በአካል እና በበየን መረብ በሚያሰለጥኗቸው ሰልጣኞች አማካኝነት ቅርኝጫፋቸውን እያሰፉ የሚገኙ ሲሆን የአለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተር ፖልን ጨምሮ የሀገር ውስጥ የጸጥታ አካላትን ትኩረት ሰበዋል።
የፍቅር ግንኙነትን በመጠቀም፣የቢዝነስ ኢሜሎችን እና ግላዊ ሚስጥሮችን በመበርበር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚያገኙት የዲጂታል አጭበርባሪዎች “ሀስል ኪንግድም፣ ያሆ ቦይስ፣ ብላክ አክስ” እና በሌሎችም መጠሪያዎች ይታወቃሉ።
አጭበርባሪዎቹ የግለሰብ እና የመንግስት የጨረታ ሂደት መረጃዎችን ጭምር በመመንተፍ በሚገኙባቸው ሀገራት ራስ ምታት ሁነዋል።
የፖስታ ሳጥን ቁጥሮች፣ የስልክ ልውውጦች፣የፋክስ እና የኢሜል አድራሻዎች፣ የማህበራዊ ዋስትና ቁጥሮች እና ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃዎች ማጭበርበሩን ለማድረግ እና ተጠቂያቸውን ለማጥመድ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል ናቸው።
“ኦንላይን ሮማንስ ስካም” ወይም የበይነ መረብ የፍቅር ማጭበርበር ተብሎ በሚጠራው ዘዴ በሀሰተኛ ስም በተከፈቱ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት ከመሰረቱ በኋላ ገንዘብ እንዲረዷቸው ወይም በጋራ ስራ እንስራ በማለት ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ አድራሻቸውን ያጠፋሉ።
ሲከፋ ደግሞ የፍቀር አጋር አድርገው በጥናት የያዙትን ሰው ግላዊ መረጃዎች፣ ፎቶ ቪድዮ እና ሌሎችንም ሚስጥሮች በማህበራዊ ትስስር ገጽ እንደሚያሰራጩ በማስፈራራት ገንዘብ የሚቀበሉበት መንገድ ይጠቀሳል።
በዚህ የማጭበርበር መንገድ ሁለቱም ጾታዊ ተጠቂዎች ሲሆኑ የሴቶች እና በእድሜ የገፉ ሰዎች ተጠቂነት ግን ከፍተኛ እንደሆነ ተነግሯል።
በዚህ መንገድ በ2023 በአሜሪካ እና አውሮፓ ከ26 ሺህ በላይ ሰዎች ተጭበርብረዋል በተመሳሳይ አመት ከአሜሪካ ብቻ 50 ቢሊየን ዶላር ድረስ ማጭበርበር ችለዋል።
ይህ መጠን ለፖሊስ ሪፖርት ከተደረገው ጥቆማ መነሻ ብቻ የተገኝ ሲሆን ለፖሊስ ያላመለከቱት እና በነዚህ አካላት የተጭበረበሩ ሰዎች ቢጨመሩ መጠኑ ከዚህም ላይ ሊጨምር እንደሚችል ነው የሚነገረው።
አጭበርባሪዎቹ አሜሪካ እና አውሮፓውያን በቀኝ ግዛት ዘመን በአፍሪካ ሀገራት ፈጸሙትን በደል እና የዘረፉትን ንብረት እያስመለሱ እንደሆነ ለደረሰው ታሪካዊ በደልም ምላሽ እየሰጠን ነው ብለው ያስባሉ።