ሩሲያ በቀጣዮቹ አምስት ዓመት ውስጥ ከኔቶ ጋር ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል ተገለጸ
ኔቶ በታሪክ ከፍተኛ ያለውን የጦርነት ልምምድ እንደሚያደርግ አስታውቋል
ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦራቸው ኔቶን እንዲያጠቃ ሊያዙ ይችላሉ ተብሏል
ሩሲያ በቀጣዮቹ አምስት ዓመት ውስጥ ከኔቶ ጋር ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል ተገለጸ፡፡
የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ ለፖለቲኮ መጽሄት እንዳሉት ሩሲያ እና ኔቶ በቀጣዮች ዓመታት ውስጥ ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም "በየዕለቱ ከሩሲያ ማስጠንቀቂያ እየሰማን ነው፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን በቀጣዮቹ ከ5 እስከ 8 ዓመታት ውስጥ ጦራቸው ኔቶን እንዲያጠቃ ሊያዙ ይችላሉ" ብለዋል፡፡
የሩሲያ ጥቃትን አሁን ላይ ይሆናል ብሎ ማሰብ ቢከብድም አውሮፓ ይህንን አስቀድመው አውቀው ዝግጅት ሊደርጉ ይገባል ሲሉም ፒስቶሪየስ ተናግረዋል፡፡
የኔቶ ወታደራዊ ኮሚቴ አዛዥ አድሚራል ሮብ ባውር በበኩላቸው ወታደራዊ ጥምረቶች ከባድ ወቅት ላይ መሆናቸውን ገልጸው ውይይቶችም ሆኑ የጦር ልምምዶች አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የስዊድን መከላከያ አዛዥ ባሳለፍነው ሳምንት ዜጎች ራሳቸውን ለጦርነት እንዲያዘጋጁ ማሳሰባቸው በሀገሬው ውጥረትን አስከትሏል፡፡
አዛዡ በኋላ በሰጡት መግለጫ ዜጎች በነግግራቸው ሊደናገጡ እንደማይገባ፣ ጦርነት ወደ ስዊድን እየመጣ መሆኑን እንዲሁም ሁሌም ሰላም ሊኖር እንደማይችል ጠቅሰዋል፡፡
ኔቶ በአስርት አመታት ውስጥ ትልቅ የተባለ ወታደራዊ ልምምድ ሊያካሂድ መሆኑን ገለጸ
በአውሮፓ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን በዩክሬን የተጀመረው ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ይዛመታል የሚል ፍራቻ እያደገ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ጦርነት በሞስኮ የበላይነት ከተጠናቀቀ ጦርነቱ ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም ሊዛመት እንደሚችል በአውሮፓ መሪዎች በኩል በተደጋጋሚ እየተሰማ ሲሆን ይህ እንዳይሆን ደግሞ ለዩክሬን የሚደረገው የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደቀጠለ ነው፡፡