ሩሲያ 63 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ በቱርክ በኩል ወደ አውሮፓ ለመላክ ማቀዷን ገለጸች
በአውሮፓ ያለው የነዳጅ ዋጋ የኔቶ አባል ሀገራት የፈጠሩት ሰው ሰራሽ ችግር እንደሆነም ሩሲያ ገልጻለች
ሩሲያ የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ ሌላ ታዳሽ ሀይል ወደ ማምረት እንደምትገባም አስታውቃለች
ሩሲያ 63 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በቱርክ በኩል ወደ አውሮፓ ለመላክ ማቀዷን ገለጸች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ካመሩ ስምንት ወራት ሊሞላው ነው።
ይህ ጦርነት በርካታ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆን ምዕራባውያን ሃገራት በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
ማዕቀቡን ተከትሎም 40 በመቶ የአውሮፓን ነዳጅ ፍላጎት ስታሟላ የነበረችው ሩሲያ ነዳጇን እንደከዚህ በፊቱ መላክ አልቻለችም።
በዚህ ምክንያት በዓለማችን የነዳጅ እና ምግብ ዋጋ የጨመረ ሲሆን በአውሮፓ ደግሞ የኢኮኖሚ አለመረጋጋቱ እየጨመረ ይገኛል።
ሩሲያ በበኩሏ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአውሮፓ ነዳጅ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን አርቲ ዘግቧል።
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አሌክሳንደር ኖቫክ እንዳሉት ሞስኮ በቱርክ በኩል 63 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ ማቀዷን ተናግረዋል።
"ቱርክ ስትሪም" የተባለው ይህ የሩሲያ አዲስ እቅድ የነዳጅ ፍላጎቱ ከጨመረ ተጨማሪ መጠን ነዳጅ እንደምትልክም ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።
በአውሮፓ ከተሞች ከፍተኛ የነዳጅ ችግር አለ የሚሉት ኖቫክ እጥረቱ በኔቶ አባል ሀገራት ምክንያት የመጣ እንደሆነም አክለዋል።
ሩሲያ የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር እንደማትፈልግ የገለጸች ሲሆን በተመጣጣኝ ዋጋ ጋዝ ለአውሮፓ እና እስያ እንደምታቀርብ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቅሰዋል
የነዳጅ እጥረት እና የዋጋ ጭማሪው በዚሁ ከቀጠለ ሩሲያ ርካሽ የታዳሽ ሀይል ወደ ማምረት እንደምትገባም ተገልጿል።