ሩሲያ የአውሮፓ ሀገራት የተፈጥሮ ጋዝ የሚያገኙበትን ማስተላለፊያ ለሶስት ቀናት ልትዘጋ ነው
ኖርድ ስትሪም፤ 167 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ማስተላለፍ የሚችል ነው
የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ መጥገና ምክንያት ሃምሌ ላይም ተዘግቶ ነበር
የሩሲያው ጋዝፕሮም ኩባንያ ፤ የአውሮፓ ሀገራት የተፈጥሮ ጋዝ የሚያገኙበትን መስመር ሊዘጋ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ አውሮፓ የሚጓጓዝበት የኖርድ ስትሪም መስመርን ነው ጋዝፕሮም ሊዘጋ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ ከሩሲያ ወደ አውሮፓ የሚገባው በኖርድ ስትሪም በኩል ቢሆንም በፈረንጆቹ ከነሃሴ 31 እስከ መስከረም ሁለት ድረስ ግን አገልግሎት አይሰጥም ተብሏል፡፡
ኖርድ ስትሪም ለሶስት ቀናት የሚዘጋው በጥገና ምክንያት መሆኑን ጋዝፕሮም አስታውቋል፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመሩ ጋዝን ከሩሲያ ወደ ጀርመን የሚያመላልስ መስመር ነበር፡፡ ድርጅቱ ለሶስት ቀናት እንደሚዘጋ ማሳወቁን ተከትሎ ጀርመን የነዳጅ ክምችቷን መቆጠብ ጀምራለች፡፡
ጋዝፕሮም የኖርድ ስትሪም ነዳጅ ማስተላለፊያን ለሶስት ቀናት እንደሚዘጋ ከገለጸ በኋላ በአውሮፓ የዋጋ ጭማሪ እንደሚከሰት ተገምቷል፡፡ ጀርመንም ይህንን ካየች በኋላ ለራሷ የሚበቃ ምርትን መቆጠብ ጀምራለች፡፡ በርሊን ቁጠባውን የጀመረችው በጋዝሮም መተማመን ስላልቻለችና እስከመጨረሻው ቢቋረጥ በሚል ስጋት መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ጋዝፕሮም መስመሩን ለሶስት ቀናት ሊዘጋ መሆኑን ማሳወቁ በአውሮፓ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተፈርቷል፡፡ ከዩክሬን ሩሲያ ጦርነት በኋላ ስጋት ውስጥ የገባው የነዳጅ ገበያ ፤ የኖርድ ስትሪም መስመር ሲዘጋ “በእንቅርት ላይ” እንዳይሆን ተፈርቷል፡፡
ጋዝፕሮም የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩን ሃምሌ ላይ ለ 10 ቀናት ዘግቶት መቆየቱ ይታወሳል፡፡ መስመሩ ከተጠገነ በኋላ መደበኛ ስራውን እንደሚጀምር ኩባንያው አስታውቋል፡፡ የኖርድ ስትሪም መስመር በቀን 167 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ማስተላለፍ የሚችል ሲሆን ከጥገና በኋላ ደግሞ 33 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ማስተላለፍ እንደሚችል ተገልጿል፡፡