አሜሪካ ለዩክሬን ለመጀመሪያ ጊዜ ሮኬቶችን ልትልክ ነው
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የ27 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያደረገችው ዋሽንግተን ተጨማሪ የ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማዘጋጀቷ ተነግሯል
ፈረንሳይም ለኬቭ የጦር ጄቶችን መላክ “ነውር የለውም” ብላለች
የሩሲያ ሃይሎች በዶኔትስክ ክልል የምትገኘውን ባክሃሙት ከተማ ለመያዝ መቃረባቸው እየተነገረ ነው።
ከተማዋን ለወራት በቦምብ ስትመታ የቆየችው ሞስኮ፥ ላይማን እና አቪዲቭካ የተሰኙ ከተሞች ላይም ጦርነቱን አጠናክራ መቀጠሏን የዩክሬን ወታደራዊ አዛዦች ገልጸዋል።
የኔቶ አባል ሀገራት ዘመናዊ የውጊያ ታንኮች ለኬቭ እንዲያቀርቡ ያሳመኑት ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪም የጦር ጄቶች በፍጥነት እንዲላክላቸው እየወተወቱ ነው።
በትናንትናው እለት ከፈረንሳይ አቻቸው ሳባስቲያን ለኮርኑ ጋር የመከሩት የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር፥ ከፓሪስ አዎንታዊ ምላሽ አግኝተዋል ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
ሳባስቲያን ላኮርኑ “ለኬቭ የጦር አውሮፕላኖችን መስጠት ነውር የለውም” ማለታቸው ተገልጿል።
አሜሪካ እና ብሪታንያ ግን ጦርነቱን መልኩን ይቀይረዋል በሚል የኬቭን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ27 ቢሊየን ዶላር በላይ ለዩክሬን ድጋፍ ያደረገችው ዋሽንግተን፥ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሮኬቶችን ለመላክ ስለማቀዷ ግን ተነግሯል።
ለዚህም የ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የድጋፍ ማዕቀፍ ማዘጋጀቷን ነው ሬውተርስ ከአሜሪካ የመከላከያ ሹማምንት አገኘሁት ያለውን መረጃ ዋቢ አድርጎ የዘገበው።
ይህም አሜሪካ እና ሩሲያ የኒዩክሌር መሳሪያ እሽቅድምድምን ለማስቆም የተፈራረሙትን ስምምነት አደጋ ላይ እንዳይጥለው ተሰግቷል፡፡
ሞስኮ ምዕራባውያኑ ለኬቭ የሚያደርጉት የጦር መሳሪያ ድጋፍ እየጨመረ መሄድ ወደ ኒዩክሌር ጦርነት ሊያስገባን ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያዋን ደጋግማ ማሰማቷ ይታወሳል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአራት ቀናት በኋላ በቻይና በሚያደርጉት ጉብኝትም አንድ አመት ሊደፍን የተቃረበውን ጦርነት ለመግታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሏል።