አሜሪካ ለዩክሬን ኤፍ-16 የጦር ጄቶችን እንደማትሰጥ ፕሬዝደንት ባይደን ገለጹ
ፖላንድ እና ፈረንሳይ ግን ለኬቭ ተዋጊ ጄቶችን ለማቅረብ ፍንጭ ሰጥተዋል
ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ እና ጀርመን መድፎችን እንደምታገኝ ቃል የተገባላት ዩክሬን ጦርነቱን ለማሸነፍ ተዋጊ ጄቶች ያስፈልጉኛል ብላለች
አሜሪካ ለዩክሬን ኤፍ-16 የጦር ጄቶችን እንደማትሰጥ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናግረዋል።
ባይደን በዋይትሃውስ ለቀረበላቸው ጥያቄ “አንልክም” የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል።
ፖላንድ እና ፈረንሳይ ግን ለኬቭ ተዋጊ ጄቶችን ለማቅረብ ፍንጭ መስጠታቸውን ነው ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ “ለኬቭ በምናደርገው ወታደራዊ ድጋፍ ውስጥ የማይካተት ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ የፈረንሳይ የጦር ጄቶች የሩሲያን መሬት እንደማይረግጡና ጦርነቱን ይበልጥ የሚያወሳስቡ እንዳይሆኑ ማረጋገጫ እንፈልጋለን ነው ያሉት።
የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ሬዥንኮቭ ዛሬ በፓሪስ በሚያደርጉት ቆይታም ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር በዚሁ ጉዳይ ይመክራሉ ተብሏል።
ፖላንድም ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ጋር በመቀናጀት መስራት እስከተቻለ ድረስ ተዋጊ ጄቶችን ለመላክ አልቸገርም ብላለች።
የፈረንሳይ እና ፖላንድ አዎንታዊ ምላሽ እንደተሰማ ግን አሜሪካ ኤፍ 16 ተዋጊ ጄቶቼን ወደ ኬቭ አልክም ስትል በፕሬዝዳንቷ በኩል ገልጻለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ግን የሩሲያን ጥቃት ለመመከት አጋር ሀገራት በፍጥነት የጦር ጄቶችን እንዲልኩላቸው መወትወታቸውን ቀጥለዋል።
ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ እና ጀርመን እንዲሁም ከጎረቤቶቿ መድፎች እንደሚላኩላት ቃል የተገባላት ኬቭ፥ ሞስኮ በምስራቅ በኩል ጥቃቱን ማፋፋሟን እየገለጸች ነው።
በመሆኑም ምዕራባውያን ቃል የገቡትን የመድፍ እና የጦር ጄቶች ድጋፍ በፍጥነት እንዲያቀርቡ ዜለንስኪ መጠየቃቸውን ነው ሮይተርስ ያስነበበው።ሞስኮ በበኩሏ የምዕራባውያኑ የጦር መሳሪያ ድጋፍ የጦርነቱን ተዋናዮች ቁጥር እንዳያበዛው ስጋቷን ገልጻለች።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “የምዕራባውያኑ ድጋፍ የኔቶ አባል ሀገራትን ይበልጥ የጦርነቱ አካል እያደረጋቸው ይሄዳል እንጂ የሚለውጠው አንዳች ነገር የለም” ማለታቸውን የሩሲያው ታስ ዘግቧል።