ዩክሬን ሩሲያ በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ እንዳትሳተፍ ጠየቀች
ዘለንስኪ የሀገራቸው አትሌቶች እየተዋጉና በጦርነቱ እየሞቱ በስፖርቱ ዓለም ገለልተኛነት ሊኖር አይገባም ብለዋል
ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የቀረበለትን የሩሲያና የቤላሩስ አትሌቶች የይወዳደሩ ሀሳብ ተቀብሏል
ዩክሬን ሩሲያ በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ እንዳትሳተፍ ጠየቀች፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ሩሲያ ከፓሪስ ኦሊምፒክ እንድትወጣ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እንደተናገሩት ሩሲያ በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ እንድትወዳደር መፍቀድ “ሽብር ተቀባይነት እንዳለው ከማሳየት ጋር እኩል ነው”።
ዘለንስኪ የሩሲያ አትሌቶችን ከፓሪሱ ውድድር ውጪ ለማድረግ በጀመሩት ዘመቻ ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደብዳቤ ልከዋል።
"ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሩሲያ አትሌቶችን ወደ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ለመመለስ የሚያደረገው ሙከራ ሽብር ተቀባይነት እንዳለው ለመላው ዓለም ለመንገር የሚደረግ ሙከራ ነው" ሲሉ ዘለንስኪ ተችተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከሩሲያ ጦር ኃይሎች የተኩስ እሩምታ እየደረሰባቸው ነው ያሏቸውን አካባቢዎች በመጥቀስ ጉዳዩ አጽንኦት እንዲሰጠው ወትውተዋል።
"ሩሲያ በኬርሰን፣ ካርኪቭ፣ ባክሙት እና አቪዲቪካ እያደረገች ያለውን ነገር አይናችሁን ጨፍናችሁ የማታዩ ይመስል" ሲሉ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ጠቁመዋል።
ሩሲያ “ውድድሩንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም የስፖርት ግጥሚያ ለግዛት ወረራ ፕሮፓጋንዳ እንድትጠቀም መፈቀድ የለበትም” ሲሉም ዘለንስኪ አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከእስያ ኦሎምፒክ ም/ቤት የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች የመወዳደር እድል ያግኙ በሚል የቀረበለትን ሀሳብ "በደስታ" ተቀብያለሁ ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሀገራቸው አትሌቶች እየተዋጉ እና በጦርነት በሚሞቱበት በዚህ ወቅት በስፖርቱ ዓለም ገለልተኛነት ሊኖር እንደማይችልም ዘለንስኪ ገልጸዋል።
ዘለንስኪ እ.አ.አ በ1936 በበርሊን የተካሄደውን ኦሎምፒክ በመጥቀስ፤ ናዚዎች በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት መደረጉን “ትልቅ የኦሎምፒክ ስህተት ነበር” ብለዋል።
"የኦሎምፒክ እንቅስቃሴዎች እና አሸባሪ ሀገራት በአንድ መንገድ መጓዝ የለባቸውም" በማለትም ከታሪክ እንማር ብለዋል።