ሩሲያ ታሊባንን ከሽብርተኝነት ዝርዝሯ ለመሰረዝ እየሰራሁ ነው አለች
ታሊባን ወደ ስልጣን የተመለሰው በአሜሪካ የሚመራው የውጭ ጦር በ2021 አፍጋኒስታንን ለቆ መወጣቱን ተከትሎ ነበር
ሩሲያ ከአፍጋኒስታኑ ታሊባን መሪዎች ጋር በወሳኝ ጉዳዮች ላይ መምከሯን ገልጻለች
ሩሲያ ታሊባንን ከሽብርተኝነት ዝርዝሯ ለመሰረዝ እየሰራሁ ነው አለች።
ሩሲያ ከአፍጋኒስታኑ ታሊባን መሪዎች ጋር በወሳኝ ጉዳዮች ላይ መምከሯን እና ታሊባንን ከሽብርተኛ ድርጅት ዝርዝር ልትሰርዘው እየሰራች መሆኗን ገልጻለች።
"ይህች ሀገር ከእኛ ቀጥሎ ያለች ነች፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እንነጋገራለን" ሲሉ የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል።
"አንገብጋቢ ጉዳዮችን መፍታት አለብን፤ይህን ለማድረግ ደግሞ ንግግር ያስፈልጋል። ስለዚህ በዚህ አግባብ አፍጋኒስታንን እየመሩ ካሉት የታሊባን መሪዎች ጋር እንነጋገራለን"
ፔስኮ "አንገብጋቢ ጉዳዮች"ን በዝርዝር አላብራሩም፤ ነገርግን ሩሲያ ባለፈው ወር በ20 አመታት ውስጥ ከባድ የተባለ የሽብር ጥቃት 144 ሰዎች ተገድለውባታል።
ለዚህ ጥቃት አይኤስአይኤስ ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን አሜሪካ ጥቃቱን ያደረሰው የአይኤስአይኤስ-ኮራሳን(አይኤስአይኬስ-ኬ) የአፍጋን ቅርንጫፍ እንደሆነ የሚያመለክት የደህንነት መረጃ እንዳላት መግለጿ ይታወሳል።
ሩሲያ ግን ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ከዩክሬን ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ክስ አቅርባለች። ነገርግን ዩክሬን እና አሜሪካ እጃችን የለበትም ሲሉ አስተባብዋል።
ታሊባን ወደ ስልጣን የተመለሰው በአሜሪካ የሚመራው የውጭ ጦር በ2021 አፍጋኒስታንን ለቆ መወጣቱን ተከትሎ ነበር። ይሁን እንጂ ቡድኑ አሁን ሩሲያ በሽብር ከፈረጀቻቸው ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ አልተሰረዘም።