ታሊባን ሴቶች በአፍጋኒስታን ውስጥ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዳይቀጠሩ ከለከለ
እገዳው አዲሱ የአፍጋኒስታን ገዥ ታሊባን ሴት ተማሪዎችን በዩኒቨርስቲዎች እንዳይማሩ ከከለከለ ከጥቂት ቀናት በኋላ ያስተላለፈው ነው
ትዕዛዙን ሳያከብር የተገኘ ድርጅት በአፍጋኒስታን የስራ ፈቃዱ ይሰረዛል ተብሏል
ታሊባን ሴቶች በአፍጋኒስታን ውስጥ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዳይቀጠሩ ከለከለ።
የታሊባን መንግስት በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኙ የውጭ እና የሀገር ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሴቶችን መቅጠር እንዲያቆሙ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ይህም የሆነው አንዳንድ ሴት ሰራተኞች እስላማዊ መሸፈኛን በትክክል ስላልለበሱ ነው ተብሏል።
እገዳው አዲሱ የአፍጋኒስታን ገዥ በሴቶች መብት እና ነጻነት ላይ እርምጃ በመውሰድ ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርስቲዎች እንዳይማሩ ከከለከለ ከጥቂት ቀናት በኋላ የተላለፈ ነው።
የአፍጋኒስታን ሴቶች እገዳውን በመቃወም በታላላቅ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፤ ታሊባን ባለፈው ዓመት ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ያልተለመደ የሀገር ውስጥ “የተቃውሞ ምልክት” ተደርጓልም።
ውሳኔው ዓለም አቀፍ ቁጣንም ፈጥሯል።
ትዕዛዙ የመጣው የምጣኔ-ሀብት ሚንስትሩ ቃሪ ዲን መሀመድ ሃኒፍ በጻፉት ደብዳቤ ሲሆን ትዕዛዙን ሳያከብር የተገኘ ድርጅት በአፍጋኒስታን የስራ ፈቃዱ ይሰረዛል ብለዋል።
የሚንስቴሩ ቃል አቀባይ አብዱል ራህማን ሀቢብ የደብዳቤውን ይዘት ለአሶሼትድ ፕሬስ አረጋግጠዋል።
ሚንስቴሩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በሚሰሩ ሴት ሰራተኞች ላይ "ትክክለኛ" ሂጃብ ባለመልበሳቸው "ከባድ ቅሬታ" ደርሶኛል ብሏል።
ትዕዛዙ በሁሉም ሴቶች ወይስ በአፍጋኒስታን ሴቶች ላይ ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል የሚለው እስካሁን ግልጽ አይደለም ተብሏል።
የአሁኑ የታሊባን እርምጃ የአፍጋኒስታን ሴቶች ከቤት እንዳይወጡ ለማድረግ መሰረት ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት ፈጥሯል።
በወጣቶች ላይ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በማስተማር በአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አሰልጣኝ የሆነችው ማሊሃ ኒያዛይ “ይህ በጣም ልብ ሰባሪ እገዳ ነው” ብላለች። "እኛ ሰዎች አይደለንምን? ለምንድነው እንደዚህ ጭካኔ የሚያደርጉት?" ስትል ስለ ሁኔታው ተናግራለች።
በካቡል የምትኖረውና በአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የምትሰራው የ25 ዓመቷ ወጣት “ስራዬ ጠቃሚ ነው ምክንያቱም ሀገሬን እያገለገልኩ እና ቤተሰቤን እየረዳሁ ነው” ብላለች። "ከዚህ ትዕዛዝ በኋላ ባለስልጣናቱ ጓዳችንን ይሞላሉ? ካልሆነ ለምን እንጀራችንን ይዘጋሉ?" ብላ ጠይቃለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔውን አውግዞ፤ ግልጽነት ለማግኘት ከታሊባን አመራር ጋር ለመገናኘት እንደሚፈልግ ተናግሯል።
"የሴቶች የራሳቸውን እጣ ፈንታ የመምረጥ ነጻነትን መንሳት፣ ማሰናከል እና ከህዝብ እና ከፖለቲካዊ ህይወት ዘርፎች ማግለል ሀገሪቱን ወደ ኋላ በመመለስ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚኖረው ማንኛውም ትርጉም ያለው ሰላም እና መረጋጋት የሚደረገውን ጥረትም አደጋ ላይ ይጥላል" ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።