የታሊባን አገዛዝ ያማረራቸው የአፍጋኒስታን ሴት አቃብያነ ህጎች በስፔን ጥገኝነት አገኙ
ታሊባን ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ 32 ሴት አፍጋኒስታናውያን አቃብያነ ህጎች ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል
የታሊባን አስተዳደር “አፍጋኒስታን የሁሉም አፍጋኒስታን የጋራ መኖሪያ ናት” ሲል የሴት አቃቢያነ ህጎች ክስ ውድቅ አድርጓል
የታሊባን አገዛዝ ያማረራቸውና በአንድ ወቅት የዴሞክራሲ ምልክቶች ተደረገው ሲታዩ የነበሩ የአፍጋኒስታን ሴት አቃብያነ ህጎች በስፔን ጥገኝነት ማግኘታቸው ተገለጸ፡፡
በስፔን ጥገኝነት አገኙ ከተባሉት 19 አቃብያነ ህጎች አንዷ የሆነቸው ኦባይዳ ሻራር ከቤተሰቧ ጋር ማድሪድ መግባቷ እፎይታ እንደሰጣት ተናግራለች፡፡
ያም ሆኖ የአፍጋን ሴቶች በታሊባን ጨቋኝ ህጎች እየተሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ ደስታ ሊሰማት እንደማችልም ገልጻለች ሻራር፡፡
"በአፍጋኒስታን ውስጥ የቀሩ አብዛኛዎቹ የአፍጋኒስታን ሴቶች እና ልጃገረዶች የመማር፣ ማህበራዊ ኑሮ የመኖር ወይም ወደ የውበት ሳሎን የመሄድ መብት የላቸውም፤ ስለዚህም ደስተኛ መሆን አልችልም"ም ብላለች ሻራር፡፡
እንደፈረንጆቹ 2021 ታሊባን የሀገሪቱን በትረ ስልጣን ዳግም መጨበጡን ተከትሎ የአፍጋኒስታን ሴቶች መብት እንደተገደበ ነው፡፡
የታሊባን አስተዳደር አብዛኞቹን ሴት የረድኤት ሰራተኞች ከስራ ከማገዱም በተጨማሪ ሴቶች እና ልጃገረዶች የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።
እንደ አፍጋኒስታን ሴቶች ሁሉ በአፍጋኒስታን ቆይታዋ ስራዋ እንኳን በቅጡ ለመስራት ተቸግራ እንደነበር የምትገልጸው ሻራር፤ አሁን ባለው ሁኔታ ሴት ዳኞች እና አቃብያነ ህጎች አስገድዶ መድፈርን እና ግድያን ጨምሮ በስርዓተ-ጾታ ወንጀሎች የተከሰሱ ሰዎችን ችሎት ሲመሩና እና የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሰጡ የዛቻና የበቀል ጥቃት ሰለባ እየሆኑ መጥተዋል ትላለች።
ይህም እሷን ጨምሮ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ምልክት ተደርገው ይወሰዱ የነበሩ 32 ሴት አቃብያነ ህጎች ሀገራቸውን ጥለው ለመሰሰደድ እንዳስገደዳቸው ተናግራለች፡፡
ለደህንነቷ በመፍራት የመጀመሪያ ስሟን ኤስ ኤም የሚል ስም የሰጠችውና አሁን በስፔን የምትገኘው ሌላኛዋ አቃቤ ህግ “በነበርኩበት ግዛት ውስጥ ብቸኛዋ ሴት አቃቤ ህግ ነበርኩ… ከታሊባን አባላት እና ወደ እስር ቤት በሚገኙ ወንጀለኞች ዛቻ ደርሶብኛል" ስትል ለሮይተርስ ተናግራለች፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገር ተናግሯል፡፡
ነገር ግን አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች የምታስተናግደው የጎረቤት ሀገር ፓኪስታን መንግስት የታሊባንን ጭቆና ፈርተው ወደ ሀገሩ ለሚመጡ አፍጋኒስታናውያንን በስደተኝነት ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተመድ ምላሽ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ፓኪስታን እንደፈረንጆቹ በ 1979 ከሶቭየት ህብረት ወረራ በኋላ እና በተከተለው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ከአፍጋኒስታን የመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች መኖሪያ መሆኗ ይታወቃል፡፡
ፓኪስታን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ብታደርግም አብዛኛዎቹ ገና አለመመለሳቸው የተመድ መረጃ ያመለክታል፡፡
ታሊባን እንደፈረንጆቹ በ2021 ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱን ለቆ የወጣ ማንኛውም አፍጋኒስታናዊ አስፈላጊውን ሂደት አሟልቶ ወደ ሀገሩ ሊመለስ ይችላል ማለቱም አይዘነጋም፡፡
በዚህም የሴት አቃቢያነ ህጎቹ ክስ ውድቅ ያደረጉት የታሊባን አስተዳደር ምክትል ቃል አቀባይ ቢላል ካሪሚ “አፍጋኒስታን የሁሉም አፍጋኒስታን የጋራ መኖሪያ ናት” ብለዋል።