ሰርጓጅ መርከቡ ሱናሚዎችን በማስነሳት ሙሉ ከተማን እንዳልነበር አድርጎ የማጠወፋት አቅም አለው
ሩሲያ ከዚህ ቀደም በዓለም ላይ ተሰምቶ የማይታወቅና ገዳይ የጦር መሳሪያ የሚታጠቅ ግዙፍ ሰርጓጅ የጦር መርከብ በቅርቡ ይፋ አድርጋለች።
ሩሲያ በቅርቡ ይፋ ያደረገችው የጦር ሰርጓጅ መርከብ "ቤልጎሮድ" የሚል ስያሜ የተሰጠው የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከብ ሲሆን፤ “የምጽአት ቀን” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።
ቤልጎሮድ የተሰኘው የሩሲያ ሰርጓጀ መርከብ 182 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ ይህም በዓለማችን ላይ ካሉ ሰርጓጅ መርከቦች ቀዳሚው እንደሚያደርገው ተነግሯል።
ማሪታይም ኤክስኪዩቲቭ ድረ ገጽ እንዳስነበበው ሰርጓጅ መርከቡ ለመንቀሳቀስ የሚረዳውን ኃይል የሚያገኘው በራሱ ላይ ከተገጠሙ ሁለት የኒውክሌር ማብላያዎች ነው።
14 ሺህ 700 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው መርከቡ ብሪታኒያ ካላት ደረጃውን የጠበቀ ነው ከተባለው ሰርጓጅ መርከብ በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ነው።
አዲሱ የሩሲያ ሰርጓጅ መርከብ በተለጣፊ መልክ በራሱ ላይ ስድስት አነስተኛ ሰርጓጅ መርከቦችን መሸከም የሚችል ሲሆን፤ መደበኛ የአውቶብስ መጠን ያላቸው ተለጣፊ ሰርጓጆቹ የኑኬሌር አረር ተሸካሚዎች ናቸው።
ቤልጎሮድ የተሰኘው የሩሲያ ሰርጓጀ መርከብ በውሃ ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ይችላል የተባለ ሲሆን፤ በ1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ኢላማን ካለበት የውሃ አካል ውስጥ ሆኖ መምታት ይችላል።
አዲሱ የሱሪያ ሰርጓጅ መርከብ ሰው ሰራሽ ሱናሚ ማእበሎችን ማስነሳት ይችላል የተባለ ሲሆን፤ እስከ 500 ሜትር ርዝመት ያለው ሱናሚ በማስነሳትም የባህር ዳርቻ ከተሞችን እንዳልነበሩ አድርጎ ሙሉ በሙሉ ማውደም ይችላል ተብሏል።
የብሪታኒያው ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ እንዳስነበበው አዲሱ የሩሲያ ሰርጓጅ መርከብ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በነጭ ባህር ላይ መታየቱን እና በወቅቱም ዲሚትሪ ዶንስኮይ የተባለ ሌላ የጦር መርከብ አብሮት እንነበረ ይታወሳል።