ሩሲያ በሰመጠችው “ሞስክቫ” ምትክ አዲስ የጦር መርከብ ጥቁር ባህር ላይ አሰማራች
አዲሷ የሩሲያ መርከብ “ማካሮቭ” የሚል መጠሪያ ያላት መሆኑ ተነግሯል
“ማካሮቭ” የጦር መርከብ ስምሪት የሩሲያን የሚሳዔል ጥቃቶች ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል የዩክሬን ጦር ሰግቷል
ሩሲያ ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር በሰመጠችው “ሞስኮቫ” የጦር መርከብ ምትክ አዲስ የጦር መርከብ ወደ ጥቁር ባህር ኦዴሳ መላኳን የዩክሬን ጦር አስታወቀ።
“ሩሲያ በጥቁር ባህር ላይ ያላትን ይዞታ እያጠናከረች ነው” ያለው የዩክሬን ጦር፤ በዚህም ከዚህ ቀደም ከነበራት ጦር መርከቦች በተጨማሪ “ማካሮቭ” የተባለ የጦር መርከብ ጥቁር ባህር ላይ አስማርታለች ብሏል።
“ማካሮቭ” የተባለው የጦር መርከብ ከሬሚያ ከሚገኘው ሴቫስፖቶል ወደብ በመነሳት ወደ ኦዴሳ አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑንም ኪቭ ኢንዲፐንደንት የተባለ ድረ ገጽ ዩክሬን ጦርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የሩሲያ የዜና ኤጀንሲ ታስ ከዚህ ቀደም የደህንነት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ባወጣው መረጃ፤ “ማካሮቭ” የተሰኘው የጦር መርከብ በጥቁር ባህር ላይ አዲሱ የሩሲያ ምልክት ይሆናል ብሏል።
“ማካሮቭ” የጦር መርከብ ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር በጥቁር ባር ላይ ላይ የሰመጠውን “ሞስክቫ” የጦር መርከብን የሚተካ ይሆናል ተብሏል።
እንደ ዩክሬን ጦር ገለጻ “ማካሮቭ” የጦር መርከብ መሰማርት ከጥቁር ባህር ላይ ወደ ዩክሬን የሚወነጨፉ ሚሳዔሎች ቁጥር ከፍ እንዳያደርገው ተሰግቷል።
የሩሲያ ብሔራዊ አርማና ብሔራዊ ኩራት ተደርጋ የምትወሰደው ግዙፏ የጦር መርከብ “ሞስክቫ” ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር በጥቁር ባሕር መስመጧን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።
‘ሞስክቫ’ የመስመጥ አደጋ ያጋጠመት፤ ባሳለፍነው በፍንዳታ ከተጎዳች ከሰዓታት በኋላ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የዩክሬን ወታደራዊ ባለስልጣናት በበኩላቸው “ሞስክቫ” የጦር መርከብ የሰመጠችው በዩክሬን በተሰራ ኔፕቱን ሚሳኤሎች ከተመታች በኋለካ ነው ብለው ነበር።