ሩሲያና ሳዑዲ አረቢያ በዩ.ኤ.ኢ ላይ የተፈፀመውን የድሮን ጥቃት አወገዙ
የየመኑ የሀውቲ አማፅያን ቡድን በትናትናው እለት በአቡዳቢ ከተማ በድሮን በመታገዝ ጥቃት ፈጽሟል
በጥቃቱ የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 6 ሰዎች ደግሞ ቀስለዋል
ሩሲያ እና ሳዑዲ አረቢያ የየመኑ የሀውቲ አማፅያን ቡድን በትናትናው እለት በተባበሩት አረብ ኢሚሬት በአቡዳቢ ከተማ በድሮን በመታገዝ የፈፀመውን ጥቃት አወገዙ።
የሳዑዲ አረቢያው ልኡል አላጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን በየመን የሚንቀሳቀሰው የሀውቲ አማፅያን ቡድን በሀገራቸው እና በዩኤኢ ላይ የፈፀመውን የሽብር ጥቃት በጽኑ ኮንነዋል።
የሳዑዲ ልዑል አልጋ ወራሽ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት መሃመድ ቢን ሰልማን ከአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ጦር ምክትል ጠቅላይ አዛዥ መሃመድ ቢን ዛይድ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅትም የሳዑዲው ልኡል አላጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰውን የሀውቲ አማፅያን ቡድን የሽብር ጥቃት በአንድነት በመቆም ሊያወግዘው ይገባል ብለዋል።
በጥቃቱ ህወታቸውን ላጡ የዩኤኢ ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ፤ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
ሩሲያ በበኩሏ በየመን የሚንቀሳቀሰው ቡድን በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ላይ በድሮን በመታገዝ የፈፀመውን ጥቃት እንደምታወግዝ አስታውቃለች።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛራኮቫ በሰጡት መግለጫ፤ በጥቃቱ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተረድተናል፤ ይሀንንም አጥብቀን እናወግዛለን ብለዋል።በአንሳር አላ የሚመራው የሀውቲ ቡድን ከዚህ አይነቱ ጸብ አጫሪ ትግባሩ እንዲቆጠብም ሩሲያ አሳስባለች።
ተባበሩት አረብ ኢሚሬት በአቡዳቢ ከተማ በትናትናው እለት በድሮን በመታገዝ በተፈፀመ ጥቃት የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ስድስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል።
በየመን የሚንቀሳቃሰው የሀውቲ አማፅያን ቡድን በአቡዳቢ በድሮን ለተፈጸመው ጥቃት “እኔ ነኝ የፈጸምኩት” ሲል ኃላፊነቱን መውሰዱም ይታወሳል።