ዩኤኢ ከአሜሪካ ጋር የተዋዋለችውን የተዋጊ ጄቶችና ድሮኖችን ግዥ ልታቆም እንደምትችል አስጠነቀቀች
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቸው ድሮኖችን ለዩኤኢ ለመሸጥ የጀመረችው ሂደት እንዲቀጥል ፍላጎት አላት ብለዋል
አቡዳቢ ከዋሸንግተን የጦር መሳሪያ ለመግዛት የ23 ቢሊየን ዶላር ውል እንደነበራት ይታወቃል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከአሜሪካን ልትገዛቸው የነበሩ ኤፍ-35 ተዋጊ ጀቶችን እና ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ግዥ ልታቆም እንደምትችል ማስጠንቀቋ ተገለጸ።
አቡዳቢ ከዋሸንግተን የጦር መሳሪያ ለመግዛት የ23 ቢሊዮን ዶላር ውል የነበራት ቢሆንም አሁን ግን ሃሳቧን ለመቀየር ማሰቧ ተገልጿል።
ሀገሪቱ ሌላ አማራጭ ማየት ስለመጀመሯ የተገለጸ ሲሆን የተዋጊ ጀቶችን እና ሌሎች ዘመናዊ ጥይቶችን ግዥ ልታቆም እንደምትችል ተልጿል።
መገናኛ ብዙኃን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከአሜሪካ ለመግዛት የተስማማችውን የ23 ቢሊዮን ዶላር የድሮን ጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ለመሰረዝ ከጫፍ መድረሷን እየዘገቡ ናቸው።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በማሌዥያ ጉብኝት ላይ ሳሉ ሀገራቸው ተዋጊ ጀቶችንና ድሮኖችን ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለመሸጥ የጀመረችውን ሂደት ወደፊት መግፋት እንደምትፈልግ ተናግረዋል ተብሏል።
ዋሸንግተን ይህንን የምታደርገው አቡዳቢ ፍላጎት ካላት እንደሆነም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
አንቶኒ ብሊንከን ይህንን ያሉት የዩኤኢ ባለስልጣን ሀገራቸው ከአሜሪካ መሳሪያ ለመግዛት የተጀመረውን ውይይት ማቆሟን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።
የዚህ የጦር መሳሪያ ግዥ ስምምነት እንዲቆም የተደረገው በቴክኒክ ችግር ምክንያት ነው ይባል እንጅ ዝርዝር ጉዳዩ አልተገለጸም።
ጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ኋይት ሃውስ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተጀመረው የጦር መሳሪያ ግዥ እንደሚጠናቀቅ ከአንድ ጊዜ በላይ ማረጋገጫ ሰጥተው እንደነበር ተዘግቧል።
ይህ ማረጋገጫ በአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን ) በኩልም የተሰጠ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ዋሸንግተን ከአቡዳቢ ጋር ያለው የጦር መሳሪያ ግዥ ጉዳይ ከየትኛውም በላይ ስትራቴጂያዊ እና ወስብሰብ ያለ እንደሆነ ገልጿል።