የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ ዩኤኢን እንደሚጎበኙ አስታወቁ
እስራኤል እና ዩኤኢ ለዓመታት ሻክሮ የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸው ይታወሳል
ቤኔት ዩኤኢን የጎበኙ የመጀመሪያው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ዛሬ እሁድ ለጉብኝት ወደ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እንደሚያቀኑ አስታወቁ፡፡
ቤኔት በስልጣን ላይ እያሉ ዩኤኢን የጎበኙ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡
‘ታሪካዊ’ የተባለው የዩኤኢ እና የእስራኤል ስምምነት
ጉብኝቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በባህረ ሰላጤው (ገልፍ) ሃገራት የሚያደርገው የመጀመሪያው ጉብኝት ነው የሚሆነው፡፡
በአቡዳቢ ከልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ዛይድ ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል፡፡
ሼክ መሃመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔት ዩኤኢን እንዲጎበኙ ባሳለፍነው ጥቅምት መጋበዛቸው የሚታወስ ነው፡፡ በእስራኤል የዩኤኢ አምባሳደር መሃመድ አል ካጃ ግብዣውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔታ ማቅረባቸውም አይዘነጋም፡፡
ሁለቱ ሃገራት ለዓመታት ሻክሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለመጀመር ከተስማሙ በኋላ በእስራኤል መሪ የሚደረግ የመጀመሪያው የዩኤኢ ጉብኝትም ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት፡፡
እስራኤል እና ዩኤኢ በአብርሃም ስምምነት በጋራ የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ለመስራት ጭምር መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
ዩኤኢ እና እስራኤል ከተስማሙ ከዓመት በኋላ የመጀመሪያዋ እስራኤላዊ ህጻን በዱባይ ተወለደች
የዛሬው የቤኔት የዩኤኢ ጉብኝት በኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ በኦስትሪያ ቬና ድርድር እየተካሄደ ባለበት ሰዓት የሚደረግ ነው፡፡
የድርድሩ አካል ያልሆነችው እስራኤል ከድርድሩ ጋር በተያያዘ ያላትን ስጋት ከመግለጽም በላይ ባለስልጣናቱ ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው የተለያዩ ሃገራት እየተጓዙ ለማግባባት በመሞከር ላይ ናቸው፡፡
ዩኤኢም ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡