በሩሲያ የተሰማሩ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በብዛት እየተገደሉ መሆናቸውን ዩክሬን ገለጸች
ከወራት በፊት ዩክሬን በተቆጣጠራችው የሩሲያ ኩርስክ ግዛት እየተፋለሙ የሚገኙት የሰሜን ኮርያ ወታደሮች ከፍተኛ ጉዳት እያጋጠማቸው እንደሆነ አሜሪካ አረጋግጣለች
ፒዮንግያነግ 10 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮቿን ለሩሲያ እንዲዋጉ እንደላከች መዘገቡ ይታወሳል
በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ለሞስኮ ተሰልፈው እየተዋጉ የሚገኙ የሰሜን ኮሪያ ጦር አባላት ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገዱ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
የዩክሬን ወታደራዊ የስለላ ተቋም ባወጣው መረጃ በኩርስክ ግዛት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ብቻ ከ30 በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መሞታቸውን እና መጎዳታቸውን ገልጿል፡፡
የስለላ ተቋሙ በኩርሰክ ግዛት በሚገኙ ሶስት አካባቢዎች በተጠቀሰው ቁጥር ልክ ወታደሮቹ እየሞቱ መሆናቸውን ማስረጃ ባላቀረበበት መግለጫው ላይ አመላክቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ በደቡባዊ ሩሲያ ድንበር ዘልቀው የገቡ የዩክሬን ወታደሮችን ለማስወጣት በሳምንቱ ሩሲያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሰሜን ኮርያ ጦር አባላትን ማሰማራቷን ተናግረዋል፡፡
በትላንትናው እለት ደግሞ የሩሲያ ወታደሮች በውግያ የሞቱ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች ማንነት እንዳይታወቅ ፊታቸውን ሲያቀጥሉ የሚያሳይ ምስል ነው ያሉትን ቪድዮ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አጋርተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከተንቀሳቃሽ ምስሉ ጋር ባጋሩት ጽሁፍ “ሩሲያ የውጭ ሀገር ጦርን ጥቅም ላይ ከማዋሏ በዘለለ ኪሳራዋ እንዳይታወቅባት ለመሸፈን እየጣረቸ ነው” ብለዋል፡፡
የዩክሬን ወታደራዊ ስለላ ተቋም “በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገደው የሰሜን ኮሪያ ጦር ከ94ኛው ብርጌድ አባላት በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ ጦሮችን በከርስክ ግዛት በማሰማራት በውግያው መሳተፉን እንደሚቀጥል መረጃ ደርሶናል” ሲል አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ፔንታጎን ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ፓት ራይደር ዋሽግተን በኩርስክ ግዛት የሰሜን ኮርያ ጦር አባላት ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገዱ እንደሚገኙ መረጃዎች እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ በጉዳዩ ዙርያ ገለልተኛ ማጣሪያዎችን ለማድረግ ባደረገው ጥረት ወደ ሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ያደረገው የስልክ ጥሪ አለመሳካቱን ገልጿል፡፡
ሞስኮ እስካሁን ከመከላከያ ጦሯ ጋር ተደባልቀው እየተዋጉ ነው ስለተባሉ የሰሜን ኮርያ ጦር አባላት በይፋ አላስተባበለችም ወይም አላመነችም፡፡
ከክሪሚሊን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላት ፒዮንግያንግ በበኩሏ ጉዳዩ ሀሰተኛ ዜና መሆኑን በመግለጽ ነገር ግን ወታደሮቿን ወደ ስፍራው ብትል እንኳን ከህግ ጋር የማየቃረን መሆኑን ተናግራለች፡፡
በባለፈው ነሀሴ ወር በድንገተኛ ጥቃት የሩሲያን ደቡባዊ ድንበር ጥሰው የገቡትን የዩክሬን ወታደሮች ለማስወጣት ከፍተኛ ውግያ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ሞስኮ በዩክሬን ጦር ተይዘው የነበሩ በርካታ አካባቢዎችን በማስለቀቅ ላይ እንደምትገኝም በቅርቡ ባወጣችው መግለጫ ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡