ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ከዘለንስኪና ፑቲን ጋር እንደሚነጋገሩ ገለጹ
ትራምፕ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስቆም የሚችል እቅድ እንዳላቸው ቢናገሩም ዝርዝር ሁኔታዎችን ይፋ አላደረጉም
ጦርነቱን በድርድር ለማስቆም ዩክሬን ግዛቷን አሳልፋ መስጠት አለባት ብለው ያምኑ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ ቀጥተኛ መልስ አልሰጡም
ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ከዘለንስኪ ፑቲን ጋር እንደሚነጋገሩ ገለጹ።
ተመራጩ የአሜሪካ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ሶስት አመት ገደማ የሆነውን ጦርነት ለማስቆም ከሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመነገመገር ዝግጁ መሆን አለባቸው ብለዋል።
"ስምምነት ላይ መድረስ አለበት" ሲሉ ትራምፕ በፍሎሪዳ የባህር ዳርቻ በሚገኘው ማ ራ ላጎ ክለብ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ግጭቱ ያስከተለውን ውድመት በሚያሳዩ ምስሎች መረበሻቸውን የገለጹት ትራምፕ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ፑቲንና ዘለንስኪን አናግራሀሉ ብለዋል።"ጦርነቱ መቆም አለበት" ብለዋል ትራምፕ።
ጦርነቱን በድርድር ለማስቆም ዩክሬን ግዛቷን አሳልፋ መስጠት አለባት ብለው ያምኑ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ ቀጥተኛ መልስ አልሰጡም።
ውዝግብ የተነሳባቸው አብዛኞቹ ግዛቶች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን እና መልሶ ለመገንባት አንድ ምዕተ አመት እንደሚወስድ ተናግረዋል።
"የቆመ ህንጻ የሌለባቸው ከተሞች አሉ፤ የፍርስራሽ ቦታ ነው" ብለዋል ትራምፕ።
ትራምፕ አክለውም ከ1861-1865 የነበረውን የአሜሪካ የእርስበርስ ጦርነት የሚያስታውስ የአስከሬን ቁልል ያለባቸውን የጦርሜዳዎች የሚያሳዩ ምስሎችን ማየታቸውን ገልጸዋል። ትራምፕ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስቆም የሚችል እቅድ እንዳላቸው ቢናገሩም ዝርዝር ሁኔታዎችን ይፋ አላደረጉም።
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በታተመው የታይም መጽሄት ቃል ምልልሳቸው ጦርነቱን የሚያስቆም "በጣም ጥሩ እቅድ" እንዳላቸው፣ ነገርግን ያለጊዜው ይፋ ካደረጉት "ጥቅም አልባ እቅድ ይሆናል"ብለው ነበር።