የሶሪያው በሽር አላሳድ ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ባወጡት መግለጫ ምን አሉ?
“ከሶሪያ የወጣሁት በውግያ ላይ የነበሩ ወታደሮች በድንገት በመሸሻቸው ነው” ብለዋል አላሳድ
የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ከ8 ቀናት የሩስያ ጥገኝነት ቆይታ በኋላ በቴሌግራም ገጻቸው ከሀገር የወጡበትን ሁኔታ ገልጸዋል
የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ደማስቆን ለቀው ከኮበለሉ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ድምጻቸው ተሰምቷል፡፡
ለ13 አመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ በሰነበተችው ሀገር የ12 ቀናት ጦርነት ከመንበራቸው ያነሳቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሶሪያን ጥሎ የመሰደድ እቅድ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ ፕሬዝዳንት በይፋዊ የቴሌግራም ገጻቸው ላይ ከቀናት በኋላ ባሰፈሩት መግለጫ፤ ደማስቆ በአማጽያን እጅ በወደቀችበት ወቅት በ”ላታኪያ” በሚገኘው የሩስያ ጦር ሰፈር የውግያ ዘመቻዎች እንዴት እየተካሄዱ እንደሆነ ለመከታተል ባቀኑበት ወቅት የሶሪያ ወታደሮች ምድባቸውን ጥለው ሲሸሹ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጦር ሰፈር አቅራቢያ በሚገኘው “ሀሜም” የአየር ሀይል መዘዣ ከፍተኛ የድሮን ጥቃት መከፈቱን ተከትሎ በአካባቢው የሰፈሩ የሩስያ ጦር አባላት ወደ ሞስኮ ይዘዋቸው እንደወጡ በጽሁፍ ባስተላለፉት ሀሳብ ላይ ገልጸዋል፡፡
መግለጫው ሲቀጥል “ደማስቆ በአማጽያኑ እጅ ከገባች ከአንድ ቀን በኋላ የመጨረሻው ወታደራዊ ይዞታዎች በመፈራረሳቸው እና የቀሩት የመንግስት ተቋማት ስራ በማቆማቸው ከወታደራዊ ካምፑ መውጣት የምንችልበት ምንም አይነት አዋጭ መንገድ አልነበር፤ በዚህ ሁኔታ ከሞስኮ ለሩስያ የጦር ካምፕ አዛዥ በተሰጠ ትዕዛዝ በአፋጣኝ ከስፍራው እንድወጣ ተደረገ” ማለታቸውን ያትታል፡፡
በተጨማሪም በእነዚህ ክስተቶች ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ከስልጣን ለመልቀቅ ወይም ጥገኝነት ለመጠይቅ አለማሰባቸውን የሚገልጹት የቀድሞው ፕሬዝዳንት፤ "መንግስት በሽብርተኞች እጅ ሲወድቅ እና ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ የማድረግ አቅሙ ሲጠፋ የትኛውም አቋም ከንቱ ይሆናል" ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ እስከ 11ኛው ሰአት ድረስ በሀገር ውስጥ እንደነበሩ ቢናገሩም ቢቢሲ በ12 ቀናቱ የሶሪያ አማጽያን ደማስቆን የመቆጣጠር ዘመቻ ወቅት ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ታይተው እንደማይታወቁ ዘግቧል፡፡
ዋና ከተማው ከቁጥጥር ውጩ በሆነበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ሊያገኟቸው ያደረጉት ሙከራ በሙሉ ባለመሳካቱ ደማስቆ በአማጽያኑ እጅ ከመግባቷ በፊት ከሀገር ሳይወጡ እንዳልቀረ እየተነገረ ነው፡፡
በሽር አላሳድ በዚህ መግለጫቸው ስለቀጣይ ህይወታቸውም ፣ ስለ ፖለቲካ ጉዟቸው እና አላማቸው ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡
የሶሪያ አማጺ ቡድኖች የሽግግር መንግስት ለመመስረት በሂደት ለይ ናቸው፤ አሳድን ለመጣል በተደረገው ውግያ ሰፊውን ሚና የተጫወተው “ኤችቲኤስ” የተባለው ቡድን የሽግግር መንግስቱን ለማቋቋም ከምዕራባውያን ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል፡፡
ሆኖም ከ2011 ጀምሮ በአሜሪካ ፣ ብሪታንያ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተፈረጀበት የአሸባሪነት ስያሜ እስካሁን አልተነሳለትም፡፡