የሩሲያ እና ኢራን ወታደራዊ ግንኙነት ለቀጣናዊ ፖለቲካ ጫና እንደማይገበር ሩሲያ ገለጸች
ሩሲያ ይህን ያለችው ኢራን ለሩሲያ እያደረገች ነው የተባለው የድሮን ሽያጭ እንድታቆም አሜሪካ ጠይቃለች መባሉን ተከትሎ ነው
ወደ ሩሲያ ድሮን መላኳን ያመነችው ኢራን የላከችው ግን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ነው የሚል ምላሽ ሰጥታለች
ሩሲያ ከኢራን ጋር የምታደርገው ወታደራዊ ግንኙነት በቀጣናዊ ፖለቲካ ጫና የማይገበር መሆኑን የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ርያብኮቭ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ኢራን ለሩሲያ እያደረገች ነው የተባለው የድሮን ሽያጭ እንድታቆም አሜሪካ ጠይቃለች መባሉን ተከትሎ ነው።
"ምንም ለውጥ የለም። ከኢራን ጋር የሚኖረው ትብብር ይቀጥላል" ብለዋል ርያብኮቭ።
"እኛ ነጻ ሀገራት ነን፤ከአሜሪካ እና አጋሮቿ በኩል ለሚመጣ ጫና እጅ አንሰጥም" ሲሉም አክለዋል።
የፋይናንሻል ታይምስ በዚህ ወር መጀመሪያ የኢራን ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የምትጠቀምባቸውን ድሮኖች ከመሸጥ እንድትቆጠብ አሜሪካ ጫና በማሳደር ላይ ትገኛለች።
ሩሲያ ባለፈው አመት ኢራን ሰራሽ የሆኑትን ሻሄድ ድሮኖች በዩክሬን ግዛት ውስጥ ዘልቃ ጥቃት ለመፈጸም ተጠቅማባቸዋለች።
ካምካዚ እየተባለ የሚጠራው ድሮን ለመብረር መንደርደሪያ ቦታ አያስፈልገውም።
ወደ ሩሲያ ድሮን መላኳን ያመነችው ኢራን የላከችው ግን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ነው የሚል ምላሽ ሰጥታለች። ሩሲያ በዩክሬን የኢራን ድሮኖችን ተጠቅማለች የሚለውን ክስ አስተባብላለች።
የኋይት ኃውስ ባለስልጣን ባለፈው ሐምሌ እንደተናገሩት ኢራን ከፈረንጆቹ ነሐሴ 2022 ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን ለሩሲያ መስጠቷን ተናገረዋል።