ዋሽንግተን እያደገ የመጣውን የኢራንን የኒውክሌር መርሃ-ግብር ስጋት ለመቀነስ የሚደረግን ማንኛውም እርምጃ እቀበላለሁ ብላለች
በዋሽንግተንና በቴህራን መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ እየተካሄደ ባለው ንግግር፤ አሜሪካ ኢራን ለሩሲያ ተዋጊ ድሮኖችን እንዳትሸጥ መጠየቋ ተሰምቷል።
ፋይናንሻል ታይምስ ለድርድሮች ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ሰማሁ ብሎ እንደዘገበው ዋሽንግተን በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ድሮኖችንና የበራሪ መገጣጠሚያ መሳሪያዎችን ለሞስኮ እንዳትሸጥ እየተጫነች ነው።
ይህ የተሰማው ሁለቱ ሀገራት ውጥረታቸውን ለመፍታት እየሞከሩ ባለበት ወቅት ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን እያደገ የመጣውን የኢራንን የኒውክሌር መርሃ-ግብር ስጋት ለመቀነስ የሚደረግን ማንኛውም እርምጃ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።
የሀገራቱ ንግግሮች እስረኞችን ለመቀያየር ከተጀመሩ ውይይቶች ጎን ለጎን ስለመደረጋቸው ታውቋል።
በዚህም ኢራን አራት አሜሪካዊያን እስረኞች ከእስር ቤት ወጥተው በቤት ውስጥ እንዲቆዩ ወስናለች።
ሮይተርስ ባለፈው ሳምንት ኢራን የተያዘባትን ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለማስለቀቅ አምስት እስረኞችን ልትለቅ እንደምትችል ዘግቧል።