ጥቃቱ በሩሲያ ውስጥ ከደረሱ ጥቃቶች ከባድ መሆኑ ተነግሯል
ሩሲያ ዩክሬን አርብ ሞስኮ ላይ የሚሳይል ጥቃት ማድረሷንና ክሬሚያን በ42 ድሮኖች መደብደቧን ተናግራለች።
ጥቃቱ እስካሁን ድረስ በሩሲያ በተያዙ ግዛቶች ውስጥ ካደረሰች ድብደባ ከባዱ ነው ተብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር "ኤስ-200" የተባለ ሚሳይል በሞስኮ አቅራቢያ መተኮሱን አስታውቋል።
"ሚሳይሉ አስቀድሞ ተለይቶ አየር ላይ እንዲመታ ተደርጓል" ብሏል።
በጥቃቱ ህይወቱ ያለፈ ሰው እንደሌለ የአካባቢው አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
ዩክሬን እስካሁን በጥቃቱ ላይ አስተያየት አልሰጠችም። ሮይተርስ እንደዘገበው ኪየቭ በሩሲያ ግዛት ውስጥ ስለምታደርሳቸው ጥቃቶች በይፋ ተናግራ አታውቅም።
ሚንስቴር አክሎም ከዩክሬን በ2014 ተገንጥላ ሞስኮን የተቀላቀለችው ክሬሚያም የጥቃት ሰለባ መሆኗን ተናግሯል።
ዘጠኝ ድሮኖች በአየር መከላከያ ስርዓት መመታቱን ገልጾ፤ ቀሪዎቹ 33 ድሮኖች ኢላማቸውን ሳይመቱ መከስከሳቸውን አስታውቋል።