ዩክሬን ስለድሮን ጥቃቱ ከመናገር ተቆጥባለች
አሜሪካ ኪየቭ ሩሲያ ግዛት ውስጥ እንድታጠቃ አልደግፍም ወይም አላበረታታም ስትል አስታውቃለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ይህን ያስታወቁት ሞስኮ በኪየቭ ተሰነዘረብኝ ያለችውን የድሮን ጥቃት አከሸፍኩ ካለች በኋላ ነው።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ሁለት የዩክሬን ድሮኖችን በአየር መከላከያ ስርዓቱ ማክሸፉን አስታውቋል።
ቃል አቀባዩ ዩክሬን ለደረሰባት "ወረራ" ራሷን እንዴት መከላከል እንዳለባት ውሳኔው የራሷ ነው ብለዋል።
ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን በማስወጣት ጦርነቱን ማስቆም እንደምትችልም አክለው ተናግረዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ከሚያዝያ ጀምሮ ዩክሬን የድሮውን ጥቃቶችን ሩሲያ ላይ ማድረሷን አጠናክራ ቀጥላለች። በቅርብ ወራት በሩሲያ መዲና ሞስኮ የሚደርሱ የድሮን ጥቃቶች እየተደጋጋሙ ነው።
ለዩክሬን የጦር መሳሪያዎችንና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በማቅረብ የምትደግፈው አሜሪካ፤ ኪየቭ በሩሲያ ግዛት ውስጥ የምትሰነዝረውን ጥቃት አልደግፍም ብላለች።
ዩክሬን በሩሲያ ግዛት አደረሰችው ስለሚባለው ጥቃት በይፋ አስተያየት ሰጥታ አታውቅም።