በሩሲያ ፈንጂዎችና ጠንካራ ምሽጎች ምክንያት የኪየቭ እርምጃ እክል ገጥሞታል ተብሏል
ዩክሬን በሁሉም ግንባሮች ከባድ ውጊያ እያደረገች መሆኑን አስታውቃለች።
ከተያዙባት ግዛቶች የሩሲያ ወታደሮችን ለማስወጣት በያዘችው ዘመቻ በደቡባዊው ምስራቅ ክፍል "አንዳንድ ስኬት" እያስመዘገበች መሆኑን ተናግራለች።
የሀገሪቱ ምክትል መከላከያ ሚንስትር ሀና ማሊር በሩሲያ ፈንጂዎችና ጠንካራ ምሽጎች ምክንያት የኪየቭ እርምጃ እክል ገጥሞታል ብለዋል።
ሆኖም የዩክሬን ጦር ዶኔትስክ አካባቢ እየገፋና በደቡብ ሁለት ግንባሮችም እያጠቃ ነው ሲሉ አክለዋል።
የዩክሬን ኃይሎች በሰኔ ወር ሲጠበቅ የነበረውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ከጀመሩ በኋላ እመርታ ማግኘታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ነገር ግን የኪየቭ ባለስልጣናት ለግስጋሴው ጠንካራ የሩስያ መከላከያ እንቅፋት እንደሆነባቸውም አምነዋል።
"መከላከያ ሰራዊቱ ሙሉ በሙሉ በፈንጂ የተቀበሩ አካባቢዎች፣ ከባድ ምሽጎችና የማያቋርጥ ድብደባ እያጋጠሙት ነው" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ዩክሬን በጦርነቱ ክፉኛ በተጎዳው ባክሙት ሁለት ስኩዌር ኪሎሜትር ስፍራ መቆጣጠሩን ምክትል መከላከያ ሚንስትሯ ገልጸዋል።
የኪየቭን የባክሙት ድል ተከትሎ ሞስኮ ጥቃት መጨመሯንም ተናግረዋል።